የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ካጃ ካላስ ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አጭር መግለጫ፣ ቀጣናዊ ግጭት መባባስ ማንንም እንደማይጠቅም ገልፀው፣ “ውይይቱን መቀጠል አለብን” በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሁለቱም ወገኖች የኒውክሌር ጉዳዮችንና ሌሎች ሰፋፊ ጉዳዮችን በተመለከተ ውይይት ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ካጃ ካላስ ጠቅሰዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ፣ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ሊኖራት እንደማይገባ በማያሻማ ሁኔታ ገልጸዋል።
በተጨማሪም እሳቸው እና የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ከኢራን ጋር የሚያደርጉትን ቀጣይ ድርድር ለማስቀጠል ከፍተኛ ጉጉት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ላሚ አያይዘውም፣ ኢራን ከአሜሪካ ጋር ውይይት እንድትቀጥል አጥብቀው ማሳሰባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ይህ ወሳኝ ወቅት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ በኢራን እና በእስራኤል መካከል በሚፈጠር ግጭት ምንም አይነት ቀጣናዊ ውጥረት እንዳይባባስ መከላከል በጣም አስፈላጊ እንደሆነም አስረድተዋል።
በታምራት ቢሻው