በአዲስ በተደራጁ ክልሎች በሚኖሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ጠንካራ የውስጥ ኅብረብሔራዊ አንድነታቸውን ለማጎልበትና በተጎራባች ክልሎች መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በነቃ የሕዝብ ተሳትፎ በዘላቂነት ማስቀጠል እንደሚገባ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ዛህራ ሁመድ ገለጹ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሰላምና የፌዴራሊዝም እሴቶች ግንባታለሕብረብሔራዊ አንድነት በሚል ርዕስ ምክክር አካሄዷል፡፡
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የኮሚኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሮክተሬት ዳይሬክተሩ አቶ ተረፈ በዳዳ ምክክሩን አስመልክቶ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ እንደገለጹት በዉይይት መድረኩ ላይ ፌዴሬሽኑን የተቀላቀሉ አዳዲስ ክልሎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተሳትፈዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ዛህራ ሁመድ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መልካም አስተዳደር ለማስፈን፣ ያልተመለሱ የመዋቅር ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታትና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሕገመንግሥታዊ ሥርዐቱን መሠረት በማድረግ ነባሩን የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በአራት ክልሎች መልሶ እንዲደራጅ ማድረጉን አስታዉሰዋል፡፡
ምክትል አፈ ጉባዔዋ መዋቅራዊ ለውጡ ለክልሎቹ የተረጋጋ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን፣ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በቅርበት ለመስጠትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በር እንደከፈተላቸውም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ መዋቅራዊ የአደረጃጀት ለውጦችን በማምጣት ፍትሐዊ የሀብት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ ልማትን ማስፋፋት፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተሳታፊነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ምክትል አፈ ጉባዔዋ ጠቁመዋል፡፡
የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት፣ የስራ እድሎችን በመፍጠር ለሰላም ግንባታ አስተዋፀኦ ማበርከትና ለግጭት መፈጠር መንስዔ የሆኑ ጉዳዮችን በመቀነስ ደኅንነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰን እና ሠላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸዉ በኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት መተግበር ከጀመረ ሦስት አስርት አመታት መቆጠራቸዉን በመግለጽ ብዝኃነትን ለማስተናገድና ለማጎልበት በተለያዩ አካላት በርካታ ተግባራት መከናወናቸዉን ተናግረዋል፡፡
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ስልጣንና ተልዕኮ መሰረት በማድረግ ስርዓቱ እንዲያድግና እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
ነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሕገ መንግሥቱን መሰረት በማድረግ በሕዝበ ውሳኔ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እና የሲዳማ ክልል በመባል በአራት ክልልሎች መደራጀቱ ይታወቃል፡
በወንድማገኝ አሰፋ