ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ካውንስል የአፍሪካ ዕጩ ሆና ተሰየመች

AMN ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም

የአፍሪካ አባል ሀገራት በአንድ ድምፅ በደረሱበት ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ በሚካሄደው የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ካውንስል ምድብ 2(Category 2) ምርጫ አፍሪካን ወክላ እንድትወዳደር በይፋ ተሰይማለች።

ይህ ታሪካዊ ስኬት ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ዘርፍ ያላትን አመኔታ፣ ተፅዕኖ እና አመራር የሚያሳይ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ነው።

ይህ ውጤት በፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ በኬንያ፣ በኡጋንዳና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተደረገ የተቀናጀ ጥረት ፍሬ ነው።

በተለይም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር ፣ የኢትዮጵያ እጩነት በአፍሪካ ደረጃ እንዲጠናከር በከፍተኛ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ በማድረግ እና ሂደቱን በቅርብ በመከታተል የላቀ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአፍሪካ ህብረት ቋሚ መልዕክተኛ፣ እና የአፍሪካ ጉዳዬች ዳ/ ጀ ከኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ከአፍሪካ አባል ሀገራት ጋር የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ጥረትን በማስተባበር ለዚህ ታሪካዊ ስኬት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

በተጨማሪም ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች፣ በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክት፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አመራርና ሠራተኞች ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት ይህ ታሪካዊ ድል ተገኝቷል።

ይህ እጩነት በሚካሄደው የICAO ካውንስል ምርጫ ኢትዮጵያ አፍሪካን በብቃትና በሀላፊነት ለመወከል ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ በአህጉሪቱ የሲቪል አቪዬሽን ልማትና ትብብር ውስጥ ያላትን አመራር የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ከትራንስፓርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review