AMN – ሐምሌ 25/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ እና የሸገር ከተማ አስተዳደሮች የ2018 በጀት ዓመት ቅንጅታዊ ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሄዱ።
በአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እና በሸገር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ጉዮ ገልገሎ መሪነት በተካሄደው በዚህ መድረክ፣ ባለፈው በጀት ዓመት በጸጥታ እና በሕግ የበላይነት ዙሪያ የተገኙ ውጤቶች ተገምግመዋል።
በውይይቱ ላይ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እንደገለጹት፤ ሕዝብን ማዕከል አድርጎ በጸጥታና በሕግ የበላይነት ዙሪያ በቅንጅት መሠራቱ ለተመዘገቡ ስኬቶች መገኘት ዋና ምክንያት ሆኗል።
በተለይም በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ወሰን አዋሳኝ አካባቢዎች የሚካሄዱ የሰላም ኮንፈረንሶች ለሰላም እሴት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን በማስፈን ሕገ-ወጥ ንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል የጋራ ቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በሁለቱም ከተሞች ያለደረሰኝ ግብይት እና የግብር ስወራን በመከላከል ረገድ የተጀመሩ ቅንጅታዊ ሥራዎች አሁንም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ሰላምና ደኅንነት ላይ ከዚህ በላቀ አቅም በመሥራት፣ በቀጣይ የሚከበሩ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ የተጀመሩ የቅንጅት ሥራዎች እንዲቀጥሉም አቅጣጫ ተቀምጧል።
የሸገር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ጉዮ ገልገሎ በበኩላቸው፣ በ2018 በጀት ዓመት ቅንጅታዊ ሥራዎች በተናበበ መንገድ መከናወናቸውን አንስተዋል።

የሕዝብን ተሳትፎ ከጸጥታ መዋቅር ጋር በማቀናጀት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫን ጨምሮ ሌሎች ሐገራዊ ተግባራት ላይ ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን እና በሁለቱ ከተሞች የጋራ ወሰን ላይ ወንጀልን በብቃት መከላከል እንደተቻለ ተናግረዋል።
በ2019 በጀት ዓመትም ይህንን ስኬት በማስቀጠል ከዚህ የተሻሉ አፈጻጸሞችን ለማስመዝገብ በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፣ ቅንጅታዊ ሥራዎችን በእቅድ መምራታቸው ቀደም ሲል የነበረውን አላስፈላጊ ቢሮክራሲያዊ ሂደት ማስቀረት እንዳስቻለ ገልጸዋል።
በዳንኤል መላኩ