AMN- ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ወንዞች ንፅህና እንዲረጋገጥ በተከናወነው ሥራ የማህበረሰቡ ቆሻሻ የማስወገድ ባህልና አቅም ማደጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ ኢንጂነር እንዳሻው ከተማ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በከተማዋ በ2018 ዓ.ም በርካታ የአረንጓዴ ቦታዎችን ማልማት ተችሏል ብለዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በበጀት ዓመቱ 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ችግኞችን ተክለናል ያሉት ምክትል ሃላፊው ዜጎችን በማሳተፍ የሚከናወነው የተፋሰስ ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በ2018 ዓ.ም 8 ወንዞች ላይ የወንዝና ወንዝ ዳርቻ የልማት ሥራዎች እንደተከናወኑ ገልጸው ከእነዚህ መካከል በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የቀበና ወንዝን ጨምሮ የቀጨኔ ወንዝ ዳርቻ፣ የአርሴማ የወንዝ ዳርቻ ተጠቃሽ መሆናቸው ተናግረዋል፡፡

ይሄም የወንዝ ዳርቻዎች የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ አዋቂዎች እና ህጻናት በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ፣ እንዲዝናኑ ከማድረግ ባለፈ አካባቢዎችም የስጋት ስፍራ እንዳይሆኑ አድርጓል፡፡
በአረንጓዴ ልማት ላይ ያለው የማህበረሰቡ ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም በመጥቀስ አረንጓዴ ቦታዎችን ለመጠበቅ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ሃላፊነት አንዳለበት አመላክተዋል።
ዜጎች አካባቢያቸውን ከብክለት እንዲጠብቁ፤ የከተማዋ ወንዞች ንጽህና እንዲረጋገጥ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር መዘርጋቱንም ምክትል ሃላፊው አንስተዋል።
እንዲሁም የወንዞች ንፅህና እንዲረጋገጥ በተከናወነ ሥራ የማህበረሰቡ ቆሻሻ የማስወገድ አቅም ማደጉን በመግለፅ ደረቅ ቆሻሻም ይሁን ፍሳሽ ወደ ወንዝ እንዳይለቀቅ ስራዎች ሲከናወኑ እንደነበር አስታውሰዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ጠባቂ እንዲሆኑ ፣ በከተማዋ የንጽህና መጠበቂያ ቤቶችንም በማስፋፋት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርገናል ብለዋል።
ኢንጂነር እንዳሻው ከተማ እንደገለፁት ፤ በከተማዋ በአረንጓዴ ልማት ላይ መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችሉ አሰራሮችም ተዘርግተዋል።
የሻምበል ምህረት