የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አመራርና ሰራተኞች ከኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ጋር በመተባበር አምስት ኪሎ በሚገኘዉ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና መስሪያ ቤት የደም ልገሳ መርሃ ግብር አካሄደዋል፡፡
አመራርና ሰራተኞቹ እንደ ሚዲያ ተቋም መረጃን ለህዝብ ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን ማህበራዊ ሃላፊነታቸዉን ለመወጣት ደም መለገሳቸዉን ተናግረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ደም የለገሱ አንዳንድ ባለሞያዎችም በተለያዩ የጤና ተቋማት የሚስተዋለዉን የደም አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ የበኩላቸዉን ሃለፊነት መወጣታቸዉን ተናግረዋል፡፡
በደም እጦት ምክንያት የአንድም ሰዉ ህይወት ማለፍ የለበትም ያሉት የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አመራርና ሰራተኞች ደም በመለገስ የዜጎችን ህይወት ከሞት በመታደጋቸዉ ደስተኛ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡
ደም መለገስ የሰብአዊነት ማሳያ በመሆኑ ለወደፊትም በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎች በመሳተፍ የበኩላቸዉን እንደሚወጡ የተናሩት ደም ለጋሾቹ ሌሎችም ደም በመለገስ ህይወትን ከሞት እንዲታደጉ ጠይቀዋል፡፡
የደም ልገሳ መርሃ ግብሩ እንደ ተቋም ለአራተኛ ጊዜ መከናወኑን የገለጹት የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ውብሸት ወልዱ አመራርና ሰራተኞቹ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ሃገራዊ ሃላፊነታቸዉን በመወጣት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
ዛሬ የተከናወነው የደም ልገሳ ፕሮግራም እንደ ተቋም ከታቀዱት የ90 ቀናት የክረምት በጎ ፍቃድ ተግባራት አንዱ መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እና የቤት ዕድሳት ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልፀዋል፡፡
በያለው ጌታነህ