ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ 2018 በጀት ዓመት የማንሰራራት ጉዟችንን የሚያፀኑ አዳዲስ እመርታዎችን ለማስመዝገብ በጋራ የምንተጋበት ዓመት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምን እንደመነሻ በመውሰድ በተዘጋጀው የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከፌደራል ተቋማት አመራሮች ጋር ዛሬ ውይይት እየተካሄደበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የ2017 በጀት ዓመት በብዙ መልኩ የኢትዮጵያ የብልጽግና ታሪክ እጥፋት ነው፡፡ዓመቱ እውነትም የኢትዮጵያ የማንሠራራት ዘመን መነሻ የሆነ ዓመት ነበር። የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድም እነዚህን መልካም አፈጻጸሞች መነሻ የሚያደርግ ነው።

በበጀት አመቱ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በማድረግ የከረሙ ስብራቶቻችን ጠግነናል፡፡ የሕዳሴ ግድብን አጠናቅቀናል፡፡ የጋዝ ፕሮጀክታችንንም እያጠናቀቅን እንገኛለን፡፡ በከተሞቻችን የጀመርናቸው የኮሪደር ልማቶች ውጤት ማምጣት ጀምረዋል፡፡ የገጠር ኮሪደርም ጀምረናል።
የ2018 በጀት ዓመት ግቦቻችንም እነዚህን መልካም አፈጻጸሞች መነሻ የሚያደርጉ፣ ካለፈው በላይ ትጋት እና ጥረት የሚጠይቁ ናቸው። ለብቻ መሮጥን ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ቅንጅትንም ይፈልጋሉ፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ በእኛ እጅ ናት፡፡ በአዲሱ በጀት ዓመት የላቁ ድሎችን በማስመዝገብ የኢትዮጵያን ማንሠራራት የሚያውጀው ትውልድ አካል እንደሆንን በማመን ለበለጠ ስኬት በትጋት መስራት ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡