ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እርሾ የሆኑ ሀገራዊ እሴቶች ወደ ገበያው መምጣት እንዳለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ” በሚል ርዕስ ተጽፎ ለአንባብያን በደረሰው መጽሀፍ ዙሪያ በተለያዩ የሥራ መስኮች የሚገኙ ባለሙያዎች እና ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች ውይይት አድርገውበታል፡፡
የጋዜጠኝነት እና ስነ ተግባቦት ባለሙያ እና ተመራማሪ አቶ ከማል ሀሺ በበኩላቸው፥ በተለይ ከለውጡ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አርአያነትን በመከተል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ያካበቱትን ልምድ እና እውቀት በመጽሀፍ መልኩ ለሕዝቡ ማካፈላቸው የሚያስመሰግን ልምምድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ” ፍለጋ በሚል ርዕስ በቅርቡ ያሳተሙት መጽሀፍ ከፍተኛ የምርምር ሥራዎች የታዩበት እና ለምንፈልገው ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ታላቅ አበርክቶ ያለው ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
የፍልስፍና ምሁር እና ተመራማሪ አቶ ዘሪሁን ተሾመ፥ ከሌሎች አገሮች በመቅዳት ዴሞክራሲን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመተግበር የተደረጉ ጥረቶች ውጤት እንዳላመጡ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህ ረገድ “ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ” በሚል ርዕስ የተጻፈው የተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) መጽሀፍ ለሀገር በቀል እውቀት ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያን የሚመስል ዴሞክራሲ ለመገንባት የሚያስችል ጥረት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ይህን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የሚገኙ የሽምግልና፣ የእርቅ፣ የሕግ እና ሌሎች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚጠቅሙ እሴቶች እንዲታወቁ የማድረጉ ስራ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡