አየር መንገዱ በአገልግሎት ጥራት እና በደንበኛ እርካታ ላይ የማይናወጥ አቋሙን በተግባር እያሳየ መሆኑን አቶ መስፍን ጣሰው ገለፁ

You are currently viewing አየር መንገዱ በአገልግሎት ጥራት እና በደንበኛ እርካታ ላይ የማይናወጥ አቋሙን በተግባር እያሳየ መሆኑን አቶ መስፍን ጣሰው ገለፁ

AMN – መስከረም 8/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገልግሎት ጥራት፣ በደንበኛ እርካታ እና በፈጠራ ላይ የማይናወጥ አቋሙን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.ኤ.አ በ2026 ለደንበኞች የሚያቀርባቸውን የበረራ ላይ ምግቦች ዝርዝር እና ቅምሻ መርሀ ግብር አከናውኗል።

በመድረኩ የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰውን ጨምሮ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በአየር ትራንስፖርት ላይ የሚቀርቡ ምግቦች የመንገደኞችን ፍላጎትና ምርጫ ያማከሉ ናቸው።

ይህ ልዩ ዝግጅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገልግሎት ጥራት፣ በደንበኛ እርካታ እና በፈጠራ ላይ ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ እንደመሆኑ መጠን የደንበኞቹን ፍላጎትና ምርጫ ባሟላ መልኩ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረው፤ ይህን ማስተናገድ የሚያስችል መሰረተ ልማት በማቋቋም እየሰራ እንደሚገኝም ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተጨማሪም ዓለም ዓቀፍ የምግብ ባለሙያዎችን በመቅጠር የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ መሆኑን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የጠቆሙት።

አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን የሚያስቀጥሉ የተሳለጡ አገልግሎቶች መስጠቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ወቅት በምግብ አቅርቦት፣ ለምግብ ደህንነት እና ለአካባቢ አስተዳደር ስርዓቶች የተለያዩ ማረጋገጫዎች እንደተሰጡትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ ጊዜያት በምርጥ የበረራ ላይ የምግብ አቅርቦት ማዕረግ ማሸነፉንና ይህ ማዕረግ ለመንገደኞች ምርጥ የበረራ ላይ ልምድ ለመስጠት የምናደርገውን ስራ እውቅና እና አድናቆት ያሳያል ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review