የአፍ እና ጥርስ ጤና አጠባበቅ

  • Post category:ጤና

AMN- ነሐሴ 8/2018 ዓ.ም

የአፍ ውስጥ ጤና ከጠቅላላ ጤንነታችን ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን ያውቃሉ?

የጥርስ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ኢዩኤል ገብሬ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የአፍ ውስጥ ጤናን መጠበቅ ከጠቅላላ ጤንነታችን ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን አብራርተዋል።

የጥርስ እና ምላስ ንጽህናን መጠበቅ፤

የጥርስ ንጽህና ሳይጠበቅ ሲቀር ጥርሶች ሊቦረቡሩ እና ለተለያዩ የድድ በሽታዎች ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ።

ከጥርስ ባለፈ ምላስን በጽዳት አለመያዝ ፈንገሶች እንዲከማቹና ለከፍተኛ የአፍ ጠረን መነሻ ምክንያት ይሆናል።

ትክክለኛው የጥርስ ማጽጃ ዘዴዎች፤

ጥርስን በቀን ሁለቴ ማፅዳት እንደሚገባ የገለጹት ዶክተር ኢዮኤል፣ በተለይም ማታ ሳያጸዱ መተኛት በባክቴሪያ መራባት ምክንያት ለአፍ ጠረን እና ለጥርስ መቦርቦር እንደሚያጋልጥ ያብራራሉ።

የጥርስ ብሩሽን አጠቃቀም በተመለከተ ሲያስረዱም፣ የጀርባውን ክፍል በ45 ዲግሪ በማዘንበል፣ የፊት ለፊቱን በክብ፣ እንዲሁም የውስጥ ክፍሎችን ከታች ወደ ላይ በማድረግ በተገቢው ማጽዳት እንደሚገባ ይናገራሉ።

የአፍ ጤና እጥረት የሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች፡

በአፍ ውስጥ የሚፈጠሩ ኢንፌክሽኖችና የጥርስ ችግሮች በደም ዝውውር አማካኝነት ወደ ልብ፣ የስኳር በሽታ እና እስከ ስትሮክ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ዶክተር ኢዩኤል አስገንዝበዋል።

ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምልክቶች፤

ውሃ በሚጠጡበት ጊዜ ጥርስን መጥዘጥዘት፣ እንዲሁም በጥርሶች ጥግ ጥግ ላይ ሻህላ መፈጠር የችግሩ መጀመሪያ መገለጫዎች በመሆናቸው ወዲያውኑ ወደ ክሊኒክ በመሄድ መታየት እንደሚያስፈልግም ዶክተሩ ያስረዳሉ።

የጥርስ ህክምና አማራጮች፤

እንደ ችግሩ ከባድነት የጥርስ እጥበት፣ ሙሌት፣ የሰርቪካል ህክምና፣ የሰው ሰራሽ ጥርስ መተካት እንዲሁም በብሬስ ወይም በኢንቪዝብል አለይነር አማካኝነት የጥርስ አቀማመጥን ማስተካከል ይቻላል።

መከላከያ መንገዶች፤

ጣፋጭ ምግቦችን ሲመገቡ የአፍ ውስጥ ንጽህናን በአግባቡ መጠበቅ፣ በቤት ውስጥ ተገቢውን የንጽህና ልምድ ማዳበር እና በዓመት እስከ ሁለት ጊዜ ወደ ክሊኒክ በመሄድ የጥርስ እጥበት ማከናወን ለአፍ ጤና መረጋገጥ ትልቅ ሚና እንዳለውም አስገንዝበዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review