ሳይነስ በሽታ ነው ወይስ የተፈጥሮ አካል? ስለ ሳይነስ ሊያውቁት የሚገባው እውነት

You are currently viewing ሳይነስ በሽታ ነው ወይስ የተፈጥሮ አካል? ስለ ሳይነስ ሊያውቁት የሚገባው እውነት

AMN- ነሐሴ 7/2018 ዓ.ም

ብዙዎች «ሳይነስ አለብኝ» እያሉ ሲታከሙ እንሰማለን፤ ይሁን እንጂ ሳይነስ በሽታ ሳይሆን በፊታችን አጥንቶች ውስጥ የሚገኝ እና እጅግ ጠቃሚ አገልግሎቶችን የሚሰጥ የሰውነት ክፍል ነው።

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከአንገት በላይ ሀኪም እና መምህር ዶክተር ኦሊያድ ታረቀኝ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሳይነስ ትክክለኛ ትርጉም፣ ለምን እንደሚጠቅም እና በጤናችን ላይ የሚያመጣቸው ተፅዕኖዎች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሳይነስ ብዙ ጊዜ እንደ በሽታ ሲነገር እንሰማለን፤ ይሁን እንጂ ሳይነስ ማለት በሰውነታችን፣ በባለቤትነቱም በፊታችን አጥንቶች ውስጥ የሚገኙ ተፈጥሯዊ የሰውነት ክፍሎች (ባዶ አየር የተሞሉ ቦታዎች) ናቸው።

በሁለቱም የፊታችን ክፍሎች ላይ (በግራ እና በቀኝ) ሳይነሶች ይገኛሉ። እነዚህም፣ ግንባራችን ላይ ግራና ቀኝ የሚገኙ፣ አይናችን ስር፣ በአይናችን መሃል ላይ ያሉ፣ ከኋላ ራስ ቅላችን ስር የሚገኙ የአየር ክፍት ቦታዎች ናቸው።

ዋና ዋና የሥራ ድርሻቸውም፣ የምንተነፍሰው አየር ተገቢው እርጥበት እና ሙቀት እንዲኖረው በማድረግ ተዋስያንና ማይክሮ ኦርጋኒዝሞች ወደ ታችኛው የአየር ቧንቧ እንዳያልፉ የማጣራት ስራ ይሰራሉ።

ስናወራ ድምፃችን ሪዞኔት (Resonate) እንዲያደርግና የተለያየ የድምፅ አወጣጥ እንዲኖረን ይረዳሉ።

ራስ ቅላችን በሙሉ ጥቅጥቅ ባለ አጥንት የተሰራ ቢሆን ኖሮ ክብደቱ በጨመረ ነበር። ባዶ መሆናቸው ድንገተኛ አደጋዎች ወይም ምቶች ቀጥታ ወደ አንጎላችን እንዳይደርሱ እንደ ሾክ አብሶርቨር (Shock Absorber) ያገለግላሉ።

የሳይነስ እና የህመም ምክንያቶች፡-

እነዚህ ተፈጥሯዊ አካላት በሚታመሙበት ወይም በሚጎዱበት ጊዜ የሚከሰተው የህመም ችግር ሳይንሳይቲስ በመባል ይታወቃል።

የሳይነስ መቆጣት ችግር ሁሉንም ሳይነሶች በአንድ ጊዜ ሊያጠቃ ይችላል። የህመሙ ዋና ዋና ምክንያቶችም፤ አለርጂ ፣ለአየር ንብረት መለዋወጥ፣ ለሽታዎች፣ ለብናኞች ወይም ለተለያዩ አካባቢያዊ ነገሮች በጀነቲክ እና በተፈጥሮ ከፍተኛ ስሜታዊነት (Sensitivity) ሲኖር የሚከሰት።

የቫይረስ ኢንፌክሽን፤ በአብዛኛው በቫይረሶች አማካኝነት የሚጀምር፣ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን፤ በቫይረስ ኢንፌክሽን ላይ ተደርቦ ሊከሰት የሚችል ተጨማሪ ችግር፣ የፈንገስ ኢንፌክሽን፤ በሳይነስ ውስጥ በብዛት ከሚታዩ ምክንያቶች አንዱ ሲሆን

ግራኑሎማተስ በሽታዎች፣አልፎ አልፎ በሰውነታችን ከሚመረቱ ንጥረ ነገሮች የተነሳ የሚከሰቱ ናቸው።

የሳይነስ ህመም ምልክቶች፡-

እንደ ህመሙ ቆይታ እና ጥንካሬ የተለያዩ ምልክቶች ሊኖሩት ይችላሉ፣ እነዚህም አፍንጫ ሁል ጊዜ ማፈን እና በጥቅጥቅ ያለ ስሜት መዘጋት፣ በአፍንጫ በኩል የሚወጡ ፈሳሾች በአለርጂ ጊዜ ቀጭን እና ውሃ የሚመስል፤ በኢንፌክሽን ጊዜ ደግሞ ወፍራም፣ ከለሩ የተቀየረ እና ጠረን ያለው፣ ፊት አካባቢ፣ ግንባር እና አይን ዙሪያ የሚሰማ የህመም እና የመወጣጠር ስሜት፣ ማስነጠስ፣ አይንና አፍንጫ አካባቢ ማሳከክ፣ አይን ዙሪያ እና ጉንጭ ስር መጥቆር (በአለርጂ ምክንያት ቆዳን ከማሸት የሚመጡ) ናቸው፡፡

ዘላቂ የሳይነስ ችግር ምልክቶች (ከሶስት ወር በላይ የቆዩ) ደግም፤ አፍንጫ ውስጥ ስጋ መብቀል እና አፍንጫ ሙሉ ለሙሉ መዘጋት፣ ደጋግሞ ነስር መምጣት፣ ከፍተኛ እና የማያቋርጥ ራስ ምታት ናቸው፡፡

የሳይነስ ሊያስከትላቸው የሚችሉ ተጨማሪ ችግሮች

ሳይነስ ህክምና ካላገኘ እና ሲባባስ ሌሎች አካላትን ሊጎዳ ይችላል፡፡ ይህም ሳይነስ ለአይን ቅርብ በመሆኑ ኢንፌክሽኑ ወደ አይን በመዛመት የመግል መቋጠር ችግር ሊያመጣ ይችላል። አጥንቶችን አሳስቶ ወደ ጭንቅላት ሊዘልቅ እና የጭንቅላት ውስጥ መግል ሊያመጣ ይችላል።

የማህለኛው የጆሮ ክፍል አብሮ በመቆጣቱ የጆሮ ውስጥ ፈሳሽ መቋጠር የጆሮ ኢንፌክሽን ሊከሰት ይችላል።

የላይኛው አየር ቧንቧ (ሳይነስን ጨምሮ) እና የታችኛው አየር ቧንቧ (ሳንባ) የስጋ ስሪታቸው ተመሳሳይ ስለሆነ፣ የሳይነስ ችግር ያለበት ሰው ለአስም ህመም ወይም ለሳምባ ግፊት ሊጋለጥ ይችላል።

የህክምና አማራጮች እና ጥንቃቄዎች፡-

የሳይነስ ህክምና እንደየ ምክንያቱ የሚወሰን ሲሆን፤ በአፍ የሚወሰዱ ወይም በአፍንጫ የሚረጩ ፀረ-አለርጂ መድኃኒቶች። አፍንጫ ውስጥ ያሉ ያባጡ ስጋዎች እንዲመናመኑ እና አየር እንዲገባ የሚያደርጉ የሚረጩ ወይም የኪኒን መድኃኒቶች እና በሀኪም ትዕዛዝ የሚሰጡ አንቲባዮቲኮችን ያካትታል፡፡

የመከላከያ እና የቤት ውስጥ እንክብካቤ ምክሮች፦

እንደ ዶክተር ኦሊያድ ገለጻ፤ ለህመሙ ማባባሻ የሆኑ ነገሮችን ቀዝቃዛ አየር፣ አቧራ፣ ኃይለኛ ሽታዎች፣ የቤት ውስጥ እንስሳት ፀጉር ወይም ሞልዶች መለየት እና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

አለርጂ በሚነሳበት ወቅት ማስክ መጠቀም፣ አፍንጫን ለማጽዳት በቤት ውስጥ የተዘጋጀ የጨው ውሀ መጠቀም ይመከራል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review