በመስከረም ወር የሚከበሩ የህዝብና የአደባባይ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለፀ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ በመስከረም ወር የሚከበሩ የህዝብ በዓላት አከባበርን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በመስከረም ወር የሚከበሩ በርካታ የህዝብና የአደባባይ በዓላትን በደመቀና በተሳካ ሁኔታ ለማክበርና ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ተደርገዋል ብለዋል።
እነዚሁ የህዝብ በዓላት ሀገራዊ እድገትን ለማምጣት እና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመስከረም ወር ከሚከበሩ የህዝብና የአደባባይ በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላትን ጨምሮ የብሔር ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የህዝብ በዓላቱን በማልማትና በማስተዋወቅ እሴታቸው ተጠብቆ በድምቀት እንዲከበሩ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዓላቱ ማህበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክሩ ወሳኝ የህዝብ ኩነቶች በመሆናቸው ለስኬታማነታቸው በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በዓላቱን፤ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ የማህበረሰቡን አብሮነት በሚያጠናክሩ መልኩ ማክበር እንደሚገባ ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ክብረ በዓላቱን በሀገር አቀፍ፥ በአህጉር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ሀገራዊ ገፅታን ለመገንባት ከመገናኛ ብዙሃን ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡