ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ ቴክኖሎጂ መር አዘማኝነት ላይ የሚያተኩረው የዲጂታል 2025 ስትራቴጂ በስኬት መጠናቀቅን ተከትሎ አሁን በበለጠ የማሽን ግብዓት (አቶሜሽን) በመጠቀም አገልግሎት አሰጣጥን የሚያጠናክረውን ዲጂታል 2030ን አስጀምረናል ብለዋል።
የፍትኅ ተደራሽነት ለዜጎች እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን እውቅና በመሥጠትም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፈጣን፣ ግልጽ እና ውጤታማ የሆነ ሥርዓት ለመገንባት በጽናት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት የፍርድ ሂደቶች በአግባቡ መቀዳታቸውን ለማረጋገጥ ድምጽን ወደ ጽሁፍ የሚቀይር ብሎም በአስተማማኝ ሁኔታ ተጠብቀው የሚቆዩበትን ስማርት የፍርድ ሥርዓት አልምቶ በመመልከቴ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።
ሥርዓቱ ፍትኅ ፈላጊዎች ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው በአካል በችሎት መገኘት ሳይጠበቅባቸው ካሉበት ሆነው ጉዳያቸውን ለመከታተል ያስችላቸዋል።
በተጨማሪም የለሙት የNetwork Operation Center እና Integrated Case Management System የፍርድ ሂደት ባለጉዳዮች በዲጂታል አውታሮች ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ያስችላሉ።
በአሁኑ ወቅት 24 የፌደራል ቅርንጫፎች በሥርዓቱ የተሸፈኑ መሆኑ አበረታች ሲሆን በቅርቡ ወደ ክልሎችም እንደሚስፋፋ ተስፋ አለን ሲሉም ገልፀዋል።