በ5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ለመሳተፍ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል

You are currently viewing በ5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ለመሳተፍ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል

AMN – ኅዳር 13/2019 ዓ.ም

ከነገ ኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) ላይ ለመሳተፍ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።

በዚህም የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ፣ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄሲካ አሉፖ እና የሩዋንዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ንሴንግዩምቫ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ፍሬሕይወት ታምሩ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) እና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል (AICC) በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ፣ ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

«የአፍሪካ የጤና ደኅንነት እና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነት እና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነት እና የማይበገር አቅም መሸጋገር» በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው ይህ ዓመታዊ ጉባኤ፤ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ሳይንቲስቶች እና የልማት አጋሮች በአህጉሪቷ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የጤና አጀንዳዎች ላይ የሚመክሩበትና ዕውቀት የሚለዋወጡበት መድረክ ነው።

በተጨማሪም ጉባኤው ቀጣናዊ ትብብርን እና ምርምርን በማሳደግ፣ በራስ አቅም ላይ የተመሠረተ የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ አፍሪካ-መር መፍትሔዎችን ለማጎልበት ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review