AMN- ኅዳር 15/2019 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዲናዋ የኢትዮጵያ የብልጽግና ተምሳሌት ከመሆን አልፋ በአፍሪካ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን ርዕይ ሰንቆ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ይህንን ርዕይ ለማሳካትም በመዲናዋ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ እያደረገ ነው።
በመንግስትና በግል ትብብር ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት እንዲገነቡ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ ገንብቶ ለአገልግሎት ያበቃውን ላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጨምሮ ሌሎቹ ሆስፒታሎች በዘመናዊና በምስራቅ አፍሪካ በማይገኙ የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሁም በብቁ የጤና ባለሙያዎች ጭምር የተደራጁ ናቸው፡፡
በዚህም በመዲናዋ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረች ትገኛለች።
ይህም ለህክምና ወደ ውጭ ሀገራት የሚሄዱ ዜጎችን ቁጥር ለመቀነስ አግዟል።
የከተማ አስተዳደሩ በመዲናዋ ግዙፍ ሆስፒታሎችንና የጤና ተቋማትን መገንባቱንና ዘመናዊ የህክምና አገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶችን ማሟላቱን ተከትሎ በርካታ የግሉ ዘርፍ ተዋንያንም ወደ ጤናው ዘርፍ እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
ይህም የከተማ አስተዳደሩ መዲናዋን ተመራጭ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ለሰነቀው ርዕይ ትልቅ አቅም ፈጥሯል፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣ የዲፕሎማሲ ማዕከል፣ አህጉርና ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች የሚካሄዱባትና የቱሪስቶች ከተማ እንደ መሆኗ መጠን፣ በመዲናዋ የሚኖሩና ወደ ከተማዋ የሚመጡ የውጭ ሀገራት ዜጎች ደረጃቸውን የጠበቁ የህክምና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ አስችሏል።

የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን እና ሌሎች ተሞክሮዎችን በማቀናጀት መዲናዋን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየሠራ ይገኛል።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም የተጀመሩ ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር፣ ለህክምና ወደ ውጪ የሚሄዱ ዜጎችን አላስፈላጊ የውጭ ምንዛሬ፣ የጊዜ እና የጉልበት ወጪ ለማስቀረት በልዩ ትኩረት እየሠራ ነው።
በወንድማገኝ አሰፋ