የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ያጎለብታል

You are currently viewing የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ያጎለብታል

AMN – ኅዳር 15/2019 ዓ.ም

«በብዝኃነት የደመቀች፤ በምክክር የጸናች ኢትዮጵያ» በሚል መሪ ሐሳብ 21ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሪት ፋይዛ መሐመድ፣ ኢትዮጵያ የራሳቸው ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግና ልማድ ያላቸው በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ተቻችለውና ተከባብረው በአንድነት የሚኖሩባት አገር መሆኗን ገልጸዋል።

በዓሉ ለጠንካራ የፌዴራል ሥርዓት ግንባታና ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት መጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በማንሳት፣ ኅብረተሰቡ ይበልጥ ለአንድነቱና ለሰላም መትጋት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው፣ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሲከበር የብዝኃ ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት ባለቤት የሆነችውን አገር ለመገንባትና የሕዝቦችን አንድነትና ሰላም ለማጠናከር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ችግሮችን በጥላቻ ሳይሆን በውይይት፣ በምክክር፣ በሕግና በመተማመን በመፍታት እንዲሁም እየተከባበሩ የጋራ ጥቅምን በማስከበር ለአገር የጋራ ዕድገት መሥራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ዝናሽ ከተማ እንደተናገሩትም፣ በዓሉ የሚከበረው የአገሪቱን ብዝኃነት፣ የሕዝቦችን እኩልነት፣ የጋራ አብሮነትና የአገራዊ አንድነት እሴቶችን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ነው።

በዓሉ የሁሉንም ሕዝቦች እኩልነትና የማንነት ክብር በማረጋገጥ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም አብራርተዋል።

መርሐ ግብሩን የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

በመሀመድኑር ዓሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review