ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነትን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚሁ ወቅት ግብጽ እና ሱዳንን ጨምሮ የተፋሰሱ ሀገራት በትብብር የሚሰሩበትን መንፈስ ቢፈጥሩ ከፍተኛ የማድግ አቅም ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
“ማንንም አካል ሊጎዳ የሚችል ስራ አናቅድም አንሰራም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአባይ ተጠቀመች እንጂ ማንንም አልጎዳችም ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ ሀይል ከማመንጨት እና የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ያለፈ አላማ እንደሌለው አንስተው፤ “ላሟን መኖ ነፍጎ ወተት ለማለብ የመሞከር ሂደት” እንደማይሰራ አሳስበዋል።
ከዚህ ባለፈ ማንኛውም አካል በኢትዮጵያ ላይ በጉልበት ፍላጎቱን ሊጭን እንደማይችልና የሚሻለው የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ትብብር መሆኑን ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ ደካማ ሆና በሁለት እግሯ መቆም እንዳትችል የሚሰሩ ሀገራት ባሉበት ሁኔታ ኢትዮጵያውያን የሀገራዊ ጥቅምን ለይተው ማወቅ እንደሚኖርባቸውም አመላክተዋል።
ለኤርትራ መንግስት ባስተላለፉት መልዕክት “ጥይት አስተላላፊ አትሁኑ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ህጋዊነትን ከተከተላችሁ አብረን ለማደግ ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ ነን” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አክለውም አሁንም ከኤርትራ መንግስት ጋር ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸው ሰላም እና ትብብርን ለሚያስቀድም ሁሉ በሩ ክፍት ነው ብለዋል።
በዳዊት በሪሁን