ዛይድ የደግነት ሩጫ ለአዲስ አበባ ድምቀትና ማህበራዊ ፋይዳ

You are currently viewing ዛይድ የደግነት ሩጫ ለአዲስ አበባ ድምቀትና ማህበራዊ ፋይዳ

AMN- ሚያዝያ 25 / 2018 ዓ.ም

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ የተዘጋጀው የዛይድ የደግነት ሩጫ የ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በታላቅ ድምቀት ተካሂዷል።

ውድድሩ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አቡ ዳቢ ከተማ በመነሳት በአሜሪካ፣ በግብፅ፣ በቻይና፣ በብራዚል እና በሀንጋሪ በተለያዩ ከተሞች የተካሄደ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2001 በአቡ ዳቢ የተጀመረው ይህ ውድድር፣ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መስራች ከሆኑት ከሼህ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያን የበጎ አድራጎት ስራዎች እና ሰብአዊነት በመነሳት ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ከበጎ አድራጎት ጋር የሚያስተሳስር ነው።

ውድድሩ በታሪኩ ከኩላሊት ህክምና እስከ ህጻናት የልብ ህክምና ድረስ ላሉ ሰብዓዊ ተግባራት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ማሰባሰብ ችሏል።

ሩጫው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መመረጡ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴነቱ ባሻገር ለከተማዋና ለኢትዮጵያ በርካታ አወንታዊ ፋይዳዎችን ያስገኛል፡፡

በአዲስ አበባ የተከናወኑት የኮሪደር ልማት እና የመንገድ መሰረተ ልማት ማሻሻያዎች መዲናዋ ለትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩነቶች ያላትን ዝግጁነት አሳይቷል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን ፣ መርሃ ግብሩ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በአፍሪካ ውስጥ ያላትን ሰብዓዊ አጋርነት ያሳየበት እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነትና ባህላዊ ትስስር ያጠናከረበት መድረክ ሆኗል።

ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት ሩጫ ያላት የላቀ ዝና ለውድድሩ የተለየ ድምቀት የሰጠው ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ወደ ከተማዋ በመሳብ የቱሪዝም ዘርፉን ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።

የዛይድ የደግነት ሩጫ ፣ ሩጫን ከቀላል ስፖርታዊ ክንውንነት ወደ ሰብዓዊነት፣ የልግስና እና የጋራ ብልጽግና ምልክት ከፍ አድርጎታል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review