አዲስ አበባ የብሪክስ ዓለም አቀፍ ጥምረት አባል አገራት ዋና ከተማ ምክር ቤቶች ጋር በትብብር ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ፈረመች

You are currently viewing አዲስ አበባ የብሪክስ ዓለም አቀፍ ጥምረት አባል አገራት ዋና ከተማ ምክር ቤቶች ጋር በትብብር ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ፈረመች

AMN-ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ አባል የሆነችበት የብሪክስ ዓለም አቀፍ ጥምረት አባል አገራት ዋና ከተማ ምክር ቤቶች ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በሩሲያዋ ዋና ከተማ ሞስኮ መፈራረማቸውን የአዲስ አበባ ም/ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር ገለፁ።

ሩሲያ ባዘጋጀችው የ2025 ዓለም አቀፍ የብሪክስ ፎረም፥ በሞስኮ ከተማ ምክር ቤት አስተባባሪነት እየተካሔደ ባለው የአባል ሀገራት ዋና ከተማ ምክር ቤቶች መድረክ የተፈረመው የግብ ስምምነት በተባበሩት መንግስታት የ2030 የልማት አጀንዳ ማዕቀፍ በከተሞች ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ፣ ትብብርን ለማጠናከር፣ ልምዶችን ለመለዋወጥና የዓለማችንን ወቅታዊ ችግሮች ለመፍታት ምክር ቤቶች የሚኖራቸውን ሚና ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ንቅናቄ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ም/ቤቱ ለኤኤምኤን በላከው መረጃ አመላክቷል።

ስምምነቱን የቻይናዋ ቤጂንግ ከተማ ምክር ቤት ከአንድ ዓመት በፊት የፈረመች ሲሆን፥ የቤላሩስ፣ የኩባ፣ የቴህራን፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የኡጋንዳ እና የሩሲያ ርዕሰ መዲና ምክር ቤቶች ዛሬ በመፈረም የፓርላማ ጥምረቱን በይፋ ተቀላቅለዋል።

ይህ ዓለም አቀፍ የጋራ ጥምረት ለአዲስ አበባ የአዲስ ምዕራፍ ምክር ቤት ታላቁ የእመርታ ማሳያ ሲሆን ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነት የተቀዳጀችውን ዲፕሎማሲያዊ ድል በማስቀጠል ከአባልነቷ የምታገኘውን ትሩፋት የሚያባዛ መሆኑም ተጠቁሟል።

ምክር ቤቱ ለዚህ ስኬት እንዲበቃ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት፣ በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ እና በሩሲያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላደረጉት ድጋፍ አፈጉባኤ ቡዜና አልከድር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review