የኑሮ ውድነትን በመቀነስ ገበያውን ለማረጋጋት ግብረ ሀይሉ የተሻለ የአሰራር ስልቶችን ቀይሶ ሊሰራ ይገባል

You are currently viewing የኑሮ ውድነትን በመቀነስ ገበያውን ለማረጋጋት ግብረ ሀይሉ የተሻለ የአሰራር ስልቶችን ቀይሶ ሊሰራ ይገባል

AMN- ህዳር 23/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ የገበያ ማረጋጋት፣ ህገወጥ ንግድ ቁጥጥር እና ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ታምርት ግብረ ሀይል የ2018 የህዳር ወር የ15 ቀን የስራ አፈጻጸም ላይ ተወያይቷል።

ውይይቱን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የግብረ ሀይሉ ሰብሳቢ አቶ ጃንጥራር አባይ እንደገለጹት፣ ግብረ ሀይሉ እቅድ አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸው፣ የተሰሩ ስራዎችን እና ያጋጠሙ ችግሮች መገምገም ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ያግዛል ብለዋል።

በውይይት መድረኩም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ያለፉት አሥራ አምስት ቀናት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

የቢሮ ኃላፊዋ በሪፖርታቸው፣ ባለፉት አስራ አምስት ቀናት ገበያውን ለማረጋጋት እቅድን ወደ መሬት በማውረድ የምርት አቅርቦትን በማሳደግ፣ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያን በስታንዳርዱ መሰረት ማስፋት፣ የገበያ ማእከላትን የመሰረተ ልማት ማሟላት፣ መደበኛ ያልሆነ የንግድ ስራ እንቅስቃሴዎች ወደ ህግ ማእቀፍ የማምጣት ስራ በመሰራቱ አበረታች ውጤት መምጣቱን ገልጸዋል።

የግብረ ሀይሉ አባላትም በቀረበው ሪፖርት ላይ የተወያዩ ሲሆን፣ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እና ገበያውን ለማረጋጋት በማምረት እና ግዥ በመፈጸም፣ የሰብል ምርቶችን በማስገባት፣ አቅዶ በመተግበር፣ ህገወጥ ንግድን በመቆጣጠር፣ የእሁድ ገበያን በማጠናከር የሚታዩ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፣ ባለፋት አስራ አምስት ቀናት የተሻለ ስራ መሰራቱን ጠቁመው፣ ለህብረተሰቡ ትክክለኛና ተጨባጭ መረጃ መስጠት፣ በሰንበት ገበያ መሸጫ ዋጋ እና አልፎ አልፎ የሚታዩ ህገወጥ ዋጋ ጭማሪ፣ ዋጋ ያለመለጠፍ ሁኔታዎችን ማረምና መረጃውን ተደራሽ በማድረግ የህብረተሰቡን ጥያቄ መመለስ እና ገበያውን ማረጋጋት የአመራሩ ቁልፍ ስራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

እቅዱ እና የሚቀርበው ሪፖርት ተጨባጭ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ምርቶችን ወደ ግብይት ማቅረብ፣ በገበያ ማረጋጋት ላይ የተሰሩ ስራዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመለክታል፡፡

አቅርቦትን ለማሳደግ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መለየትና ችግራቸውን መፍታት፣ የማህበራትን ጥያቄ በመፍታት ምርት እንዲያከማቹ ማድረግ፣ በከተማ ግብርና የተሰሩ ስራዎች ወደ ገበያ እንዲወጡ ማድረግ እንዲሁም የምሽት ንግድ እንቅስቃሴና የህግ ማስከበሩን ስራ በትኩረት እንዲሰሩም አቶ ጃንጥራር አባይ አሳስበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review