ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ እድገት፣ ዘላቂ ልማትን እና የሰራተኞች ክብርን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኗን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
37ኛው የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ስብሰባ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከህዳር 23 እስከ 25 ቀን 2018 ዓ/ም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ተወካዮች በተገኙበት የሰራተኞች ማህበራት ስብሰባዎች፣ የልምድ ልውውጦች፣ የስራ ጉብኝቶች እና የአለም አቀፉ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን(ITUC) ምክርቤት በተገኙበት የሚካሄድ ይሆናል።
በመርሀ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ አደም ፍራህ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ እያከናወነች ያለው የእድገት ግስጋሴ የሰራተኞችን መብት ያከበረ እና የሁሉምን ዜጎች ተሳታፊነት የጠበቀ እንዲሆን ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልፀዋል።
ለዚህም በተለያዩ መስኮች ያመጣችው ለውጥ በዘርፉ ላላት ጅማሮ ውጤታማነት ማሳያ ነው ብለዋል።
በመርሀግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው አለማችን በበርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውጥረት ውስጥ ብትሆንም በዚ ሁሉ ውስጥ የሰራተኞች መብት እንዲከበር መሰል መሰባሰቦች ከፍተኛ አበርክቶ አላቸው ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የሠራተኛ ማኅበራት ተወካዮችን ጨምሮ ከ150 በላይ ሀገራት የተወጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
ጉባኤው በማህበራቱ መካከል ያለውን መልካም የሥራ ግንኙነት ከማጠነከር ባለፈ ለሀገሪቱ የገፅታ ግንባታ አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑም ታምኖበታል።
በቤተልሔም አየነው