አርሰናል ከብሬንትፎርድ የዛሬው ተጠባቂ ጨዋታ

You are currently viewing አርሰናል ከብሬንትፎርድ የዛሬው ተጠባቂ ጨዋታ

AMN ኅዳር 24 ቀን 2018 ዓ.ም

በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት መርሃግብር ዛሬ ስድስት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። አርሰናል ብሬንትፎርድን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል።

መድፈኞቹ በቼልሲ ከጣሉት ነጥብ ለማገገም ሦስት ነጥቡ ያስፈልጋቸዋል። የነጥብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ያጠበበው ማንችስተር ሲቲን ለመራቅም ጨዋታ ወሳኝ ነው። አርሰናል ብሬንትፎርድ በገጠመባቸው ስምንት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በአምስቱ የበላይነቱን አሳይቷል፡፡

ብሬንትፎርድ ወደ ፕሪምየር ሊግ ባደገበት 2021 2ለ0 ያሸነፈበት ጨዋታ መድፈኞቹ ላይ ያሳካው ብቸኛ ድሉ ነው፡፡

በዛሬው ጨዋታ በአርሰናል በኩል አጥቂው ቪክቶር ዮኬሬሽ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስዊድናዊው አጥቂ ከጉዳቱ ካገገመ በኋላ በቼልሲው ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ 20 ደቂቃ መጫወቱ ይታወሳል፡፡

በቼልሲው ጨዋታ ያልተሳተፉት ሊአንድሮ ትሮሳርድ እና ዊሊያም ሳሊባ ዛሬም መግባታቸው አልተረጋገጠም፡፡

በኤምሬትስ የሚደረገው ጨዋታ ምሽት 4፡30 ሲል ይጀምራል፡፡

በተመሳሳይ ሰዓት ብራይተን ከአስቶንቪላ ፣ በርንሌይ ከክሪስታል ፓላስ እንዲሁም ወልቭስ ከኖቲንግሃም ፎረስት ይጫወታሉ፡፡

ምሽት 5፡15 ላይ በሂደት እየተሻሻለ የመጣው ቼልሲ የዋንጫ ተፎካካሪነቱን ለማስቀጠል ከሜዳው ውጪ ሊድስ ዩናይትድን ይገጥማል፡፡

ከአስከፊ የውጤት ማጣት ጉዞ በኋላ በሳምንቱ መጨረሻ ዌስትሃምን ያሸነፈው ሊቨርፑል ዛሬም ሌላ ድል ለማግኘት ሰንደርላንድን ይገጥማል፡፡ በዌስትሃሙ ጨዋታ ተጠባባቂ የነበረው ሞሐመድ ሳላህ በዛሬው ጨዋታ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ይመለሳል የሚለውን ለማየት ያጓጓል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review