ከቀይ ባህር እየተገፋን፣ ከአባይ እየሸሸን የኖርነው በምን ምክንያት ነዉ? – ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

You are currently viewing ከቀይ ባህር እየተገፋን፣ ከአባይ እየሸሸን የኖርነው በምን ምክንያት ነዉ? – ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

AMN – ታኅሳስ 10/2018 ዓ.ም

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች “ከቀይ ባህር እየተገፋን፣ ከአባይ እየሸሸን የኖርነው በምን ምክንያት ነው”? ሲሉ ዕይታቸውን አካፍለዋል።

ቀደም ባሉት ግዜያት ኢትዮጵያ በፍትሐዊ መንገድ የተፈጥሮ ፀጋዎቿን እንዳትጠቀም በርካታ ስራዎች በእጅ አዙር መሠራታቸውን አንስተዋል።

በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘውን የቀይ ባህር ጨምሮ ከዓባይ ውሃ ተጠቃሚነት በመግፋት የኢኮኖሚ ጥንካሬዋን የማዳከም ስራዎች በተለያየ መንገዶች ሲሰሩ እንደነበር አንስተዋል።

ማህበረሰቡ ለወንዝና ለውሃ ተፋሰስ የተዛባ አመለካከት እንዲኖረው የተሰራው ስራ ጉልህ ሚና እንደተጫወተም ለከያንያኑ አብራርተዋል።

ለአብነትም የወንዝ ዳርቻዎችን የወንጀል ድርጊት መፈፀሚያ፣ የድሆች መኖሪያ፣ ህገወጥ ግንባታ ማከናወኛ ብሎም የአጋንት መጠራቀሚያ አርጎ በመሳል አመለካከት ላይ ቀደም ባለው ትውልድ ላይ ተሰርቷል ብለዋል።

በአንፃሩ ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታው ወንዝና የውሃ ተፋሰስ ስፍራዎች የመዝናኛ፣ የቅንጡ ቤቶች መገኛ እና የሀብታሞች መኖሪያን ጨምሮ ከተማም ጭምር የሚገነባው በእዚሁ ስፍራ መሆኑ ምን ያህል የአመለካከት ክፍተት ለመፍጠር እንደተሰራብን ማሳያ ነው ይላሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት።

ይህ የተዛባ ትርክት ለዘመናት በአባይ ውሃ ተጠቃሚነት እና በቀይ ባህር ላይ ጥያቄ እንዳይነሳ አሉታዊ ተፅዕኖን ቢያሳድርም፣ ኢትዮጵያዊ አንድነትና ዓለም አቀፍ ተሰሚነትን በማጠናከር የህዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ ድል ማድረግ ተችሏል፤ የቀይ ባህር ጥያቄም በትውልዱ በሰፊው እየተነሳ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል።

በሚካኤል ኅሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review