የተገነቡ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች የትራፊክ ፍሰትን በማቃለልና ስርቆትን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው

You are currently viewing የተገነቡ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች የትራፊክ ፍሰትን በማቃለልና ስርቆትን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው

‎AMN ታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም

‎በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፣ ለከተማዋ የትራፊክ ፍሰት መሻሻል እና ለተሽከርካሪዎች ደህንነት መጠበቅ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተገለጸ።

‎በተለይም የተቀናጁ የመኪና ማቆሚያዎች (ፓርኪንጎች) እና ዘመናዊ የታክሲና የአውቶቡስ ተርሚናሎች መገንባታቸው በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የነበሩ ስር የሰደዱ ችግሮችን እየቀረፉ መሆኑን ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው  የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች  ገልጸዋል።

አቶ ኤርሚያስ ከበደ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናቸው የኮሪደር ልማቱ ከመከናወኑ በፊት የነበረውን ከአሁኑ ጋር በማነጸፀር  ቀደም ሲል በመንገዶች ላይ በነበረው ከፍተኛ መጨናነቅ ምክንያት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ አደጋ ይደርስ እንደነበር ገልጸዋል ይህም ለትራፊክ አደጋ መበራከት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል ብለዋል ።

‎የሚኒባስ አሽከርካሪው አቶ ቢተው ሰለሞን በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል የፓርኪንግ ቦታ ባለመኖሩ አሽከርካሪዎች መኪናቸውን ደርበው ለማቆም ይገደዱ እንደነበርና ይህም መንገዶችን ይዘጋ እንደነበር አስታውሰዋል።

‎አሁን ግን በኮሪደር ልማቱ የተገነቡት  በተለይ በየመንገድ ዳር ወረፋ ይይዙ የነበሩ ታክሲዎች በነፃነትና ያለምንም የሰዓት ገደብ አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

‎በመገናኛ አካባቢ የፓርኪንግ ሰራተኛ የሆነችው ምስራቅ ካሳዬ፣ ቀደም ሲል በነበረው የመንገድ ዳር ፓርኪንግ ስርቆትና ግጭት ይበዛ እንደነበር ጠቅሳ፤ አሁን ግን ባለንብረቶች በሙሉ እምነት ንብረታቸውን አስቀምጠው እንደሚሄዱ ተናግራለች።

‎አሽከርካሪው አቶ ኪዳኔ ክንዱም ከዚህ ቀደም መኪናቸውን መንገድ ዳር አቁመው በመሄዳቸው፣ ቴፕና ስፒከር እንደተሰረቀባቸው አስታውሰው፣ አሁን ግን የፓርኪንግ ቦታዎቹ ዋስትና እየሰጧቸው መሆኑን ገልጸዋል።

‎የትራፊክ ባለሙያው ኢንስፔክተር ጋሻሁነኝ ሙሉጌታ፣ የትራፊክ መጨናነቁ መቀነሱ በተለይ አምቡላንሶችና ታካሚዎችን የያዙ ተሽከርካሪዎች በፍጥነት እንዲንቀሳቀሱ ዕድል መፍጠሩንና የትራፊክ ፖሊሶችን ድካም መቀነሱን አብራርተዋል

‎የአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳሬክተር አቶ ኤሊያስ ዘርጋ፣ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በኮሪደር ልማቱ ከ70 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችሉ የፓርኪንግ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን ገልጸዋል።

‎ይህም ቀደም ሲል በመብራትና በአደባባዮች አቅራቢያ የሚቆሙ ተሽከርካሪዎች በሲግናል ኦፕሬሽን ላይ ይፈጥሩት የነበረውን እክል መቅረፉንና የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻሉን አረጋግጠዋል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review