በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ በ18 ሳይቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው

You are currently viewing በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ በ18 ሳይቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው

AMN- ታኀሣሥ 22/2018 ዓ/ም

በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ በ18 ሳይቶች የግንባታ ሥራ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር መኮንን ሚጄና ገልጸዋል፡፡

የግንባታ ሥራውንም የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በጋራ በመሆን ማስጀመራቸውን ኢንጂነር መኮንን ሚጄና ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ሳይቶቹ ባለፉት 6 ወራት ግንባታ መጀመራቸውን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ አሁን ላይ አፈፃጸማቸው ባልተለመደ ሁኔታ ባለ 9 ወለል ላይ የደረሱ ግንባታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከ6 እስከ 8 ዓመታት ይፈጁ የነበሩ ግንባታዎች አሁን በ6 ወራት ውስጥ እስከ 9 ወለል መገንባት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

የተቋራጭ፣ የአማካሪ፣ የቢሮው እና የኮርፖሬሽኑ ባለሙያዎች ሳይት ላይ ተገኝተው የሥራ ባህልን በቀየረ ሁኔታ 24/7 እየሰሩ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና ሁሉንም ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም አብራርተዋል፡፡

በዚህም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎችን ታሳቢ በማድረግ፣ በከተማዋ ዝቅተኛ ዋጋ ካላቸው ቤቶች ጀምሮ ኪራይ ቤት እና ከፍተኛ ድጎማ የተደረገበት የቤት አቅርቦት ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ሳይቶች ከተጠናቀቁ በኋላ መሠረተ ልማቶችን የመዘርጋት ልምድ እንደነበር ያነሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ አሁን ግን በከተማ አስተዳደር ደረጃ የመሠረተ ልማት ክላስተር አደረጃጀት ተቋቁሞ ህግ ተዘጋጅቶለት ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም መሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት በጋራ አቅደው ፕሮጀክቱን ለመጨረስ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review