ከሕገ-ወጥ እርድ የጸዳና በሐኪም የተረጋገጠ ሥጋን ለሕዝብ ማቅረብ የሚያስችል ኅብረት ተመሠረተ

You are currently viewing ከሕገ-ወጥ እርድ የጸዳና በሐኪም የተረጋገጠ ሥጋን ለሕዝብ ማቅረብ የሚያስችል ኅብረት ተመሠረተ

AMN | ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም.

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት እና በሸገር ከተማ የሚገኙ ቄራዎች ኅብረት የመመስረቻ የስምምነት ሰነድ የመፈራረሚያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል።

ኅብረቱ በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት እና በሸገር ከተማ በሚገኙ ስምንት ቄራዎች መካከል የተመሠረተ ሲሆን፣ በዘመናዊ መልኩ ጤንነቱ በባለሙያ ሐኪሞች የተረጋገጠ የከብት፣ የበግ፣ የፍየል፣ የአሳማና የግመል ሥጋን እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ ቆዳና ሌጦን፣ ብሎም ከእርድ የሚገኘውን ተረፈ ምርት በጥራት ለገበያ የማቅረብ ተልዕኮን አንግቦ የተመሠረተ መሆኑ ተገልጿል።

ሕገ-ወጥ እና ጤናው ያልተጠበቀ እርድ የአዲስ አበባንና የሸገር ከተሞችን ሲፈትን መቆየቱ በመርሐ ግብሩ ላይ ተነስቷል። ኅብረቱ ይህንን ችግር ከመቅረፍ ባለፈ፣ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚያስችል እና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሥጋ የሚያመርት ኩባንያ እንደሚያቋቁም ተነግሯል።

ኅብረቱ ከአምስት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ከሕገ-ወጥ እርድ የጸዳ፣ በቄራዎች ውስጥ ብቻ የተመረተ፥ የተመረመረ ሥጋ እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ ተረፈ ምርት ለገበያ እንዲቀርብ በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቋል።

በመቅደስ ደምስ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review