AMN – ሐምሌ 26/2018 ዓ.ም
በእርግዝና ወቅት ከሚያሳስቡ የጤና ስጋቶች መካከል በህብረተሰቡ ዘንድ «ሾተላይ» በመባል የሚታወቀው የእናትና ፅንስ የደም አይነት አለመጣጣም አንዱ ነው።
ይህ ችግር በተለይ የደም አይነታቸው አር ኤች አሉታዊ (Rh-negative) በሆኑ ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄን ይሻል።
የደም አይነቶች በዋናነት በ A፣ B፣ AB እና O እንዲሁም በእያንዳንዳቸው ውስጥ በሚገኙት አር ኤች ፖዘቲቭ እና አር ኤች ኔጌቲቭ የሚከፈሉ ሲሆን፤ አር ኤች ፕሮቲን በቀይ የደም ሴል ላይ ሲኖር አር ኤች ፖዘቲቭ፣ ከሌለ ደግሞ አር ኤች ኔጌቲቭ ተብሎ ይጠራል።
በአለም አቀፍ ደረጃ ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ አር ኤች ፖዘቲቭ ሲሆን፣ ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆነው ብቻ አር ኤች ኔጌቲቭ ነው።
ሾተላይ የሚከሰተው እናት አር ኤች ኔጌቲቭ ሆና አባት አር ኤች ፖዘቲቭ በሚሆንበት ጊዜ እንዲሁም አር ኤች ፖዘቲቭ የሆነ ፅንስ ሲፀነስ ብቻ ነው።

በእርግዝና ወቅት በተለያዩ አጋጣሚዎች የደም መፍሰስ ሲያጋጥም የፅንሱ ደም ወደ እናት የደም በመቀላቀል ከልጁ ቀይ የደም ሴል ላይ የሚገኙት ፕሮቲኖች በእናትየው በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት እንደ ባዕድ ነገር ይታዩና መከላከያ ፀረ-እንግዳ አካላት ማምረት ይጀምራሉ።
ፀረ-እንግዳ አካል ለማምረት የተወሰነ ጊዜ ስለሚፈጅ እና አብዛኛው የደም ንክኪ የሚፈጠረው በወሊድ ሰዓት በመሆኑ በመጀመሪያው እርግዝና ላይ ምንም አይነት ችግር አይፈጥርም፤ በተከታታይ የሚረገዘው ፅንስ አር ኤች ኔጌቲቭ ከሆነም ምንም ስጋት የለውም።
ነገር ግን ቀጣዩ ፅንስ አር ኤች ፖዘቲቭ በሚሆንበት ጊዜ ቀደም ብሎ ተመርቶ የተቀመጠው ፀረ-እንግዳ አካል ፅንሱን ማጥቃት ይጀምራል።
ይህ የተፈጠረ ፀረ-እንግዳ አካል የእንግዴ ልጁን በማለፍ የፅንሱን ቀይ የደም ህዋስ ሲያጠቃ የፅንስ የደም ማነስ፣ የልብ ድካም፣ በሰውነት ውስጥ ውሀ መቋጠር፣ የፅንስ ውርጃ፣ እንዲሁም ከተወለደ በኋላ የህፃን ቆዳና አይን ቢጫ መሆን የመሳሰሉ አደገኛ ችግሮችና ሞትን ያስከትላል።

የደም አይነት አለመጣጣምን በዘመናዊ ህክምና ሙሉ በሙሉ መከላከል እና ማከም የሚቻል ሲሆን፤ ለዚህም ስኬት የቅድመ-እርግዝና እና የቅድመ-ወሊድ ክትትል ወሳኝ ሚና አለው።
ሴቶች ከማርገዛቸው በፊት ወይም ካረገዙ በኃላ የደም አይነታቸውን ማወቅ የሚኖርባቸው ሲሆን፣ እናቲቱ Rh-negative መሆኗ ከታወቀ በደምዋ ውስጥ ፀረ-ሰው መፈጠር አለመፈጠሩን በየጊዜው መቆጣጠር ይቻላል።
የእናቲቱ አካል የልጁን አወንታዊ የደም ሴሎች አውቆ ፀረ-ሰው እንዳያመነጭ የሚከላከል መርፌ በ28ኛው የእርግዝና ሳምንት፣ ህፃኑ ከተወለደ በኋላ የልጁ ደም አዎንታዊ ሆኖ ሲገኝ፣ እንዲሁም ማንኛውም የደም መፍሰስ ወይም የፅንስ ማቋረጥ አደጋ ሲያጋጥም ይሰጣል።
ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ ሰውነቱ ቢጫ ከሆነ ወይም የደም ማነስ ከታየበት የፎቶቴራፒ ሕክምና በመጠቀም ወይም አስፈላጊ ከሆነ የደም ዝውውር በማድረግ ህፃኑን ሙሉ በሙሉ ማዳን ይቻላል።
በበረከት ጌታቸዉ