AMN-ሐምሌ 29/2018 ዓ.ም
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የህዝብ ልሳንነቱን በላቀ ጥራትና ይዘት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሠለሞን ዲባባ ገልፀዋል።
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2019 እቅድ ወይይት ያካሄደ ሲሆን በበጀት አመቱ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አመራርና ሰራተኞችም እዉቅና ሰጥቷል፡፡
ተቋሙ ጥራት፣ፈጠራና ፍጥነትን ባማከለ መልኩ በተለያዩ የይዘት አማራጮችና ቋንቋዎች በተለያዩ ቻናሎች የትውልድ ድምፅ በመሆን ስኬታማ ስራዎች እየሰራ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሠለሞን ዲባባ ገልፀዋል።
የከተማዋ ዋና የመረጃ ምንጭ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የተቋሙን አሰራር፣ የይዘት ጥራት እና የቴክኖሎጂ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ሥራዎችንም በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

ተቋሙ የከተማዋን እንቅስቃሴ በጥራት ለማድረስ ቴክኖሎጂዎችን ለማሟላት በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት የተቋሙን የስም፣ የሞቶ እና የምስል ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እያዘጋጀ መሆኑንም አንስተዋል።
በይዘት በኩልም እንደ ዋርካና አገልጋዩ ያሉትን ፕሮግራሞች በመደገፍ ሀገራዊ መግባባትን የመገንባት ኃላፊነቱን የሚወጡ ጥልቅና ተፅዕኖ ፈጣሪ የምርመራ ዘገባዎች ላይ ትኩረት ይደረጋልም ብለዋል።

ተቋሙ በ2018 አፈፃፀሙ የይዘት ተደራሽነትን እንዲሁም የይዘት ጥራትን ከማሳደግ ረገድ በበጀት ዓመቱ እንደ ከተማ የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ ችሏል።
በሚካኤል ህሩይ