ኮሚሽኑ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ተወያየ

AMN ታህሳስ 24/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጋር ዛሬ በፅሕፈት ቤቱ ተወያይቷል፡፡

በውይይቱ ንግግር ያደረጉት ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) በሀገራችን ዘመን የተሻገሩ አለመግባባቶች መፍትሔ እንዲያገኙ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን አስታውሰዋል፡፡

በአዋጅ ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ የካቲት 14/2014 ዓ.ም የተቋቋመው ኮሚሽኑ አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ ኢትዮጵያዊያን በምክክሩ እንዲሳተፉ በማድረግ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ዋና ኮሚሽሩ ገልፀዋል፡፡

እንደ ዋና ኮሚሽሩ ገለፃ ኮሚሽኑ በተለይ በሀገሪቱ በሚገኙ 1 ሺ 234 የተለያዩ ወረዳዎች ከሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ከክልል እና ከተማ አስተዳደር ባለድርሻ አካላት፣ ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከዲያስፖራው አጀንዳ እንዳሰባሰበ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የሀገራዊ ምክክር ሂደትን ለማስጀመር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ንግግር እያደረገ መሆኑን ጠቁመው ሂደቱን ለማስጀመር የተለያዩ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የትግራይ ክልል የምክክር ሂደት እንደተጠናቀቀ የሀገራዊ የምክክር ጉባኤውን መጀመር የኮሚሽኑ ቁልፍ ተግባር መሆኑንም ዋና ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎች ኮሚሽኑ የቀሩትን ተግባራት በእቅዱ መሰረት እንዲከውን እንደ ማህበረሰብ መሪነታቸው ከኮሚሽኑ ጎን በመሆን እገዛ እንዲያደርጉ ዋና ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎችም ኮሚሽኑ ያከናወነውን ሥራ አድንቀው፣ ቀሪ ተግባራቱን ከዳር እንዲያደርስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማረጋገጣቸዉን ከኮሚሽኑ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review