አርሰናል ከ ሊቨርፑል ፦ መድፈኞቹ ወርቃማውን እድል ለመጠቀም የሚያደርጉት ጨዋታ

You are currently viewing አርሰናል ከ ሊቨርፑል ፦ መድፈኞቹ ወርቃማውን እድል ለመጠቀም የሚያደርጉት ጨዋታ

AMN ታኅሣሥ 30 ቀን 2018 ዓ.ም

አርሰናል ካደረጋቸው 20 የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት የገጠመው በሁለቱ ብቻ ነው።

ከእነዚህ ሁለት ሦስት ነጥቡን ከወሰዱበት ቡድኖች አንዱ የሆነው ሊቨርፑል ዛሬ ኤምሬትስን ይጎበኛል። መድፈኞቹ የመጀመሪያ ዙሩን ሽንፈታቸው ቁጭት ከመወጣት በላይ ሦስት ነጥቡ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። ትናንት ምሽት ማንችስተር ሲቲ እና አስቶንቪላ ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ የዛሬው ድል በስምንት ነጥብ እንዲርቁ እድል ይሰጣቸዋል።

የዛሬውን ጨምሮ 18 ጨዋታ እየቀረው ይህን ልዩነት መፍጠር ለመድፈኞቹ ትልቅ የራስመተማን ስንቅ ይሆናቸዋል።

ከሌሎቹ በተሻለ እያሳዩት ያለው ወጥ የሆነ ብቃት እንዲሁም ጠንካራው የቡድን ስብስባቸው ከ22 ዓመት በኋላ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት መሰረት ይሆናቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

አርሰናል በአስቶንቪላ ከተረታ በኋላ በሁሉም ውድድር ያደረጋቸውን ሰባት ተከታታይ ጨዋታ አሸንፏል። እስካሁን በሜዳው ኤምሬትስም ሽንፈት አልቀመሰም። የዛሬ ተጋጣሚው ሊቨርፑል ግን ባለፈው ዓመት የሊጉ አሸናፊ ሲሆን የሰራውን ተዓምር ለመድገም ተቸግሯል።

ድል ሲያረግ እንኳን አሳማኝ ብቃት የማያሳየው የመርሲሳይዱ ክለብ በውድድር ዓመቱ ስድስት የሊግ ጨዋታ ተሸንፏል። ዛሬ ሰባተኛው ሽንፈት ከመጣ ከመሪው አርሰናል በ17 ነጥብ ይርቃል።

ሁለቱ ክለቦች በዕለተ ሀሙስ ሲጫወቱ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም እኤአ 1947 አንፊልድ ላይ ተገናኝተው አርሰናል 3ለ1 ማሸነፍ እንደቻለ የኦፕታ መረጃ ያሳያል።

አርሰናል በፕሪሚየር ሊጉ ብዙ ጨዋታ ካሸነፉት ቡድኖች አንዱ ግን ሊቨርፑል ነው ። ቀዮቹ በፕሪምየር ሊጉ አርሰናልን 26 ጊዜ መርታት ችሏል። መድፈኞቹ ሌላ ብዙ የተሸነፉት በማንችስተር ዩናይትድ ሲሆን በተመሳሳይ በ26 ጨዋታ ተረተዋል። በዛሬው ጨዋታ በአርሰናል በኩል አዲስ የጉዳት ዜና የለም።

ሊቨርፑል ሁጎ ኢኪቲኬን መልሶ ማግኘቱ ገና አልተረጋገጠም። አሌክሳንደር ኢዛክም የተገዳባቸው አርነ ስሎት ኢኪቲኬን ካላገኙ በፉልሃሙ ጨዋታ እንዳደረጉት ኮዲ ጋክፖን በዘጠኝ ቁጥር ቦታ ሊያጫውቱ ይችላሉ።

ግቦች የማይጠፉት የሁለቱ ክለቦች ተጠባቂ ጨዋታ ምሽት 5 ሰዓት በኤምሬትስ ይከናወናል። አንቶኒ ቴይለር ደግሞ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመራሉ።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review