ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ 90 ዓመታትን ባስቆጠረ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ ከሰማይ ሰማይ እየተወረወሩ የጠላትን አከርካሪ በመስበር ሀገርን ከነ ክብሯ ማስቀጠል የቻሉ ቆራጥ ጀግኖች ተፈጥረዋል።
አንዳንዶቹ ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ታሪክ ፅፈው በመስዋዕትነት ሲለዩ በህይወት የቆዩት ደግሞ የፈፀሙትን ጀብድ ዛሬም ድረስ ለትውልድ ይተርካሉ።
ከሐምሌ 14 ቀን 1969-የካቲት 1970 ዓ.ም በተካሄደው የኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት በኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎች አለምን ያስደመመ ገድል የተፈፀመበት ነው።
በወቅቱ የሶማሊያ አየር ኃይል ዘመናዊ የተባሉ ሚግ-23 አውሮፕላኖችን ታጥቆ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ደግሞ ከሚግ -23 ጀት በሶስት እጥፍ ያነሱ ጥቂት F-5E የተሰኙ አውሮፕላኖችን ታጥቆ ነበር ወደ ጦርነቱ የገባው።
ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎች የአየር ውጊያ ብቃትና የሀገር ፍቅር ወኔ ጋር ተዳምሮ በብዙ እጥፍ አውሮፕላኖችን የታጠቀው የሶማሊያ አየር ኃይል በአየር ለአየር ውጊያ አከርካሪው ተሰብሮ ጦርነቱ ካራማራ ላይ በድል ተደመደመ። የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጀግንነትም በአፍሪካ ሰማይ አስተጋባ።
የጀግኖቹ ገድል ዛሬም ድረስ በትውልድ ቅብብሎሽ ውርስ ሆኖ ቀጥሏል። በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነትም ሆነ በፀረ ሽብር ዘመቻ እና በህግ ማስከበር ዘመቻ ለነፍሳቸው ሳይሳሱ በሰማይ እንደ ሻማ እየቀለጡ በደማቸው ታሪክ የፃፉ ሀገር ወዳድ ተተኪ ጀግኖች ተፈጥረዋል።
በመስዋዕትነታቸው ሀገርን እየዋጁ ሰንደቅ አላማችንን በድል ብስራት ከፍ አድርገው አውለብልበዋል። ዛሬም የአንበሶቹ ሰማይ በንስሮቹ አይን እየተጠበቀ ነው።
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በትውልድ ቁጭት በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ የለውጥ ጉዞን የጀመረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለታላቅ ሀገር በሚመጥን መልኩ እየተገነባ ሲሆን “የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነትና የአንድነት ምልክት” በሚል መሪ ቃል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉንም ከጥር 15-19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ያከብራል።
የታላላቅ ሀገራት አየር ኃይሎች የሚሳተፉበት የ”ጥቁር አንበሳ” የአየር ትርዒት የበዓሉ ድምቀት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ጀግኖችን እናክብር ጀግኖችን እንፍጠር!! -የኢትዮጵያ አየር ኃይል