“ይቻላል” በሚል መንፈስ ለአሸናፊነት መዘጋጀት ለሀገር ከፍታ ቁልፍ ጉዳይ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing “ይቻላል” በሚል መንፈስ ለአሸናፊነት መዘጋጀት ለሀገር ከፍታ ቁልፍ ጉዳይ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN-ሚያዝያ 17/2018 ዓ.ም

ራስ ኃይሉ ስፖርት፣ ትምህርትና ሥልጠና ማዕከል አስፈላጊው ጥገና ተደርጎለት ዛሬ በይፋ ተመርቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳናች አቤቤ በማዕከሉ ምረቃ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል ተመርቆ የነበረ ቢሆንም የገጠሙትን ቴክኒካዊ ክፍተቶች ኮንትራክተሩ በድጋሚ ገብቶ እንዲያስተካክላቸው መደረጉን ገልጸዋል።

አሁን ላይ ማዕከሉ በላቀ ጥራት ታድሶ በተሟላ ሁኔታ አገልግሎት መስጠት በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።

ይህ መሠረተ ልማት ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ትልቅ ብስራት መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ ማዕከሉ በዋናው ዘርፍ በየመንደሩ ተደብቀው የቀሩ ተሰጥኦዎችን በማውጣት ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን አቅም ለዓለም እንድታሳይ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

መሠረተ ልማቱ መሟላቱ ከተማዋ የተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የዋና ውድድሮችን እንድታስተናግድ እንደሚያስችላትም አክለዋል።

በቅርቡ ከተከፈቱት የስፖርት ፓርኮች በተጨማሪ ይህ ማዕከል መከፈቱ ለስፖርተኞች ሰፊ አማራጭን ይዞ መጥቷል።

“ትውልዱ ዕድል ነው ያጣው” ያሉት ከንቲባ አዳናች፣ መሰረተ ልማቶች በተሟሉ ቁጥር ለሀገር ኩራት የሚሆኑና ራሳቸውን ከፍ የሚያደርጉ ብቁ ዜጎችን ማፍራት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ማዕከላት መኖሩ በወጣቶች ዘንድ መነሳሳትን፣ ትልቅ ራዕይንና የመልካም ውድድር መንፈስን እንደሚያዳብርም አስገንዝበዋል።

ወጣቶች ከአልባሌ ቦታዎች በመራቅ በከተማዋ የተስፋፉትን የእግር ኳስ ሜዳዎች፣ ጅምናዚየሞችና አጠቃላይ የስፖርት ፓርኮችን በመጠቀም ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲለውጡ ጥሪ አቅርበዋል።

አካልንና አእምሮን እያዳበሩ “ይቻላል” በሚል መንፈስ ለአሸናፊነት መዘጋጀት ለሀገር ከፍታ ቁልፍ መሆኑንም ከንቲባዋ ገልፀዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review