•29 የመንገድ ፕሮጀክቶች በራስ ሀይል ግንባታቸው እየተከናወነ ይገኛል
“የመንገዱ ግንባታ ከተጀመረ አራት ዓመት ያህል ቢሆነውም እስከአሁን አላለቀም፡፡ በየጊዜው እየተጀመረ ሲቋረጥ ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በእንቅስቃሴያችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል፡፡ በበጋው አቧሯ ይቦንብናል፡፡ በክረምት ደግሞ ጭቃና አደባባይ አካባቢ አስፋልት ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ጎርፍ ይገድባል፡፡” ይላሉ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ጎፋ መብራት ኮንዶሚኒየም ነዋሪ የሆኑት አቶ ሙራድ ከድር፡፡
በአሁኑ ወቅት ከጎፋ ካምፕ አንስቶ እስከ መብራት ሀይል ኮንዶሚኒየም የሚገነባው የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታው እየተፋጠነ በመሆኑ ደስ ብሎኛል፡፡ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ገፅታ በመቀየር፣ የንግድና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
በሙያቸው አሽከርካሪ የሆኑት የአካባቢው ነዋሪ አቶ አሸናፊ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ መንገዱ ከዚህ ቀደም በከፊል ኮብልስቶንና አስፋልት የነበረ፤ ለእግረኛና ተሽከርካሪ የማይመች ነበር። መንገዱን በዘመናዊ መልኩ አስፋልት ለማልበስ የግንባታ ስራ ቢጀመርም ረጅም ጊዜ ሳያልቅ ተጓትቶ መቆየቱን ይናገራሉ፡፡
“መንገዱ በመቆፋፈሩ በበጋ አቧራ፤ በክረምት ወቅት ደግሞ ጭቃ ስለሚኖር ወደ ቤታችን ለመግባትና ለመውጣት ስንቸገር ቆይተናል፡፡ በመብራት ሀይል ኮንዶሚኒየም በኩል ባለው መስመር በስራ መውጫና መግቢያ ሰዓት የትራፊክ መጨናነቅና አንዳንድ ጊዜ አደጋ ያጋጥም ነበር፡፡” ሲሉ አቶ አሸናፊ ያጋጠማቸውን ችግር ያስረዳሉ፡፡ የመንገዱ መጠናቀቅ በአካባቢው ያለውን የትራፊክ እንቅስቃሴ በማቃለል ረገድ ከፍተኛ ጥቅም ያለው በመሆኑ ግንባታውን ማፋጠን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በመንገዱ ዳርቻ የሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ከፍተው እየሰሩ የሚገኙት ወይዘሮ ሰሚራ ነጋሽ የመንገድ ግንባታው መጓተት በስራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡ “መንገዱ በመቆፋፈሩ፤ ሰው እንደ ልብ አይንቀሳቀስም፤ ስራችን ተቀዛቅዟል፤ በኪሳራ ነው ስንሰራ የቆየነው፡፡ የመንገዱ መጠናቀቅ በአካባቢው ያለውን የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች በማነቃቃት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
በመብራት ሀይል የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪ የሆኑትና በሬስቶራንት ስራ የተሰማሩት አቶ በረከት ይመር እንዲሁ መንገዱ ተቆፍሮ ለዓመታት ሳይሰራ በመቆየቱ በነዋሪዎች እንቅስቃሴና በግልም የንግድ ስራቸው እንዲቀዛቀዝ በማድረግ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮባቸው ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግንባታው እየተፋጠነ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ይበቃል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ኢንጂኒዬር አበባው አለምነህ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የደቡብ አዲስ አበባ መንገድ ፕሮጀክት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ከሚገነባቸው መንገዶች መካከል ከጎፋ ካምፕ እስከ መብራት ሀይል ኮንዶሚኒየም ያለው የመንገድ ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡ የመንገድ ፕሮጀክቱ አንድ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ (988 ሜትር) ርዝመት ይሸፍናል፡፡ በግራና ቀኝ አምስት አምስት ሜትር የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 20 ሜትር ስፋት አለው፡፡ ሁለት ቦታዎች ላይ የታክሲና የአውቶቡስ መቆሚያ ግንባታዎችን ያካተተ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱ በህዳር ወር 2014 ዓ.ም ተጀምሮ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲያልቅ ዕቅድ ተይዞለት ሀዚ በተሰኘ የሀገር ውስጥ ተቋራጭ ተጀምሮ ነበር። ነገር ግን ተቋራጩ በተሰጠው ጊዜ ከላይ ያለውን አፈር በማንሳት የመሙላት እንዲሁም 300 ሜትር የሚደርሰው የመንገዱ አካል ላይ የቱቦ ቀበራ ስራ ብቻ ነው ያከናወነው፡፡ ተቋራጩ አፈጻፀሙ ደካማ በመሆኑና የነዋሪዎች እሮሮ ምክንያት እየሆነ በመምጣቱ ከተቋራጩ ጋር የነበረው ውል እንዲቋረጥ ተደርጎ ከህዳር 12 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በራስ ሀይል አቅም እየተገነባ ይገኛል፡፡

ኢንጂኒዬር አበባው እንደገለፁት፣ የመንገድ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ 156 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ነው ወደ ስራ የተገባው፡፡ በአሁኑ ወቅት በመንገዱ በግራና ቀኝ 800 ሜትር የሚሸፍን የማፋሰሻ ቱቦዎችን የመቅበር ስራ ተከናውኗል፡፡ የሙሊት ስራ፣ ከቄራ እና መብራት ሀይል የሚመጣውን ውሃ ተቀብለው በአግባቡ ማስተናገድ የሚያስችሉ ማፋሰሻዎች እንዲሁም በየ20 ሜትር የመሬት ውስጥ መስመሮች መግቢያ ተከፋች ክዳኖች (ማንሆሎችን) የሚቀመጡባቸው ስፍራዎችን የማዘጋጀት ስራ ተከናውኗል። የፕሮጀክቱ ግንባታ አፈፃፀም 32 በመቶ ደርሷል። በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ውስጥም በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡
ከጎፋ ካምፕ እስከ ጎፋ መብራት ሀይል ኮንዶሚኒየም የነበረው መንገድ ከዚህ ቀደም የተወሰነው ክፍል ኮብልስቶን እና ሌላው በአስፋልት የተሰራ፤ የተበላሸና የተጎዳ በመሆኑ ለተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ምቹ አልነበረም፡፡ የመንገዱ መጠናቀቅ ይኸንኑ ችግር ይፈታል፡፡ ከዚህም ባሻገር አሽከርካሪዎች ከጀርመን አደባባይ በኩል ከጎፋ ካምፕ ወደ መብራት ሃይል ኮንዶሚኒየም ከዚያም ወደ ሳሪስና ላፍቶ በአቋራጭ ለመሄድ ያገለግላል፡፡ ከቄራና መብራት ሃይል ባሉት መንገዶች የሚመጣው ጎርፍ በአግባቡ ማፋሰሻ ስላልተሰራለት ለእንቅስቃሴ እክል ፈጥሮ ነበር፡፡ ግንባታው ለዚህ መፍትሔ እንደሚፈጥር ነው ኢንጂኒዬር አበባው የተናገሩት፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በራስ ሀይል የሚገነባቸው መንገዶች የመንግስትን ጊዜና ወጪን በመቆጠብ፣ የስራ ዕድል በመፍጠር፣ የዕውቀት ሽግግርን በማሳደግ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው እንደሆኑም አክለው ገልጸዋል፡፡
በራስ ሀይል መንገዶችን የመገንባት ጥረት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን የመገንባት፣ የመጠገንና የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ነው፡፡ የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ ሰለሞን ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ ባለስልጣኑ በዋናነት የመንገድ ግንባታ ስራዎችን በሁለት መንገድ ያከናውናል፡፡ አንደኛ ተቋራጮች ጋር ውል በመግባት (በኮንትራት) እንዲገነቡ ያደርጋል። ሁለተኛ በራስ ሃይል አቅም የመንገድ ግንባታዎችን ያከናውናል፡፡
ባለስልጣኑ በራስ ሀይል እያከናወነ ባለው የመንገድ ግንባታ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን አቶ ኢያሱ ያብራራሉ፡፡ አንደኛውን የመንገድ ኔትዎርክ ከሌላኛው ጋር የሚያስተሳስሩ፣ አጭርና አቋራጭ መንገዶች በፍጥነትና በጥራት መገንባት አስችሏል፡፡ በተጨማሪም በኮንትራት አፈፃፀም ሂደት ችግር የገጠማቸው መንገዶች፤ ውል በሚቋረጥበት ጊዜ እንዳይዘገዩ በብዙ ቦታዎች በራስ ሃይል ፈጥኖ በመግባትና በማጠናቀቅ መንገዶች ለአገልግሎት እንዲውሉ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡
አቶ ኢያሱ እንደገለፁት፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመንገድ ግንባታን በራሱ አቅም ማከናወኑ በመንገድ ግንባታዎች ከጊዜና ወጪ አኳያ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመፍታት ትልቅ አቅም ፈጥሯል። በራስ ሀይል ለሚገነባቸው መንገዶች ግብአት መሆን የሚችሉ ምርቶችን በራሱ አቅም ያመርታል፡፡ ይህም ወጪንና ጊዜ በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
የመንገድ ግንባታ ስራዎች በተቋራጮች ሲሰሩ የተወሰኑት በሀገር ውስጥ ገንዘብ እና ሌሎች ደግሞ በውጭ ምንዛሪ የሚገነቡ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ በራስ አቅም የሚገነቡ መንገዶች የውጭ ምንዛሪን በማዳን ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው አቶ ኢያሱ ተናግረዋል፡፡

ባለስልጣኑ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት በቅርቡ ሪፎርም ያካሄደ ሲሆን በሪፎርሙም የአሰራር ማሻሻያ፣ አዳዲስ የአሰራር ስርዓት የመዘርጋት፣ የሰው ሀይል መልሶ የማደራጀት ስራዎች በራስ ሀይል አቅም ለሚገነባቸው መንገዶች ትልቅ ጥቅም አላቸው፡፡ ከአደረጃጀት አኳያ ቀደም ሲል አምስት የሚደርሱ የመንገድ ግንባታና ሁለት የመንገድ ጥገና አገልግሎቶች የነበሩ ሲሆን እነዚህን ወደ አስር አድርሷል፡፡ ይህም ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች በመግባት በፍጥነት ስራዎችን ለመፈፀም አቅም ፈጥሯል። በአሁኑ ወቅትም የመንገድ ሀብት አስተዳደሩን በአምስት ሪጂኖች (በሰሜን፣ ደቡብ፣ ምዕራብ፣ ምስራቅና ማዕከላዊ አዲስ አበባ) በማደራጀት የመንገድ ሀብት ከመንገድ ጥገና፣ የመንገድ ጥገናውን ከመንገድ ግንባታው ጋር አስተሳስሮ መስራት የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
ባለስልጣኑ በራስ ሀይል የሚያከናውናቸውን ስራዎች በአግባቡ ለመስራት የመሳሪያ አቅርቦት ወሳኝ ሲሆን በዚህ ረገድ በየጊዜው ትላልቅና ለተለያየ ግንባታ የሚውሉ ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎችን በማሟላት አቅሙን እያጠናከረ መጥቷል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ከጃፓን መንግስት ከ80 በላይ ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች በድጋፍ አግኝቷል፡፡ እነዚህ የተቋሙን የመፈፀም አቅም በማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን አቶ ኢያሱ ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ባለስልጣኑ 17 የአስፋልት፣ 6 የኮብልስቶን፣ 4 የጠጠር መንገዶች እንዲሁም የድጋፍ ግንብ ስራዎች፣ የድልድይና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ግንባታ ጨምሮ በአጠቃላይ 29 ፕሮጀክቶች በራስ ሀይል አቅም እያከናወነ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት ዙር በተከናወነው የኮሪደር ልማትም ባለስልጣኑ በራሱ አቅም ሰፋፊ ስራዎችን አከናውኗል፡፡ ለምሳሌ በሁለተኛው ምዕራፍ ካዛንቺስ፣ ከአንበሳ ጋራዥ እስከ ጎሮ አደባባይ፣ ከሳር ቤት- ሀይሌ ጋርመንት-ፉሪ የኮሪደር ልማትና ሌሎች ቦታዎች ትልቅ ተሳትፎ አድርጓል፡፡
አቶ ኢያሱ እንደሚገልፁት፣ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በራስ ሀይል የመንገድ ፕሮጀክቶችን የመገንባት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ በመምጣቱ የከተማ አስተዳደሩ በርካታ ስራዎች በራስ ሀይል እየተሰሩ ነው፡፡ ለአብነትም የወንዞች ዳርቻ ልማት በተሰራባቸው አካባቢዎች ያሉ መንገዶች የተገነቡት በባለስልጣኑ አቅም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በግንባታ ላይ በሚገኘው የቦሌ ብራስ – አትላስ የኮሪደር ልማት ግንባታ የመንገድ ግንባታ እያከናወነ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በ2017 በጀት ዓመት 13 የሚደርሱ መንገዶችን በማጠናቀቅ ለምርቃት አብቅቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል ስምንቱ በራስ ሀይል አቅም የተገነቡ ናቸው። ይህም የተቋሙን የመፈፀም አቅም እንደሚያሳይ አቶ ኢያሱ ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር በተቋራጮች የአፈፃፀም ድክመት የተጓተቱ መንገዶች በሚኖሩበት ጊዜ፤ ውል እንዲቋረጥ በማድረግ በራስ ሀይል በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ እያደረገና እየሰራ ይገኛል፡፡ መንገዶች ግንባታቸው ተጀምረው በፍጥነት የማያልቁ ከሆነ በትራፊክ ፍሰት፣ በንግድና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በአፈፃፀም ድክመት ምክንያት ውሉ እንዲቋረጥ ተደርጎ፤ በባለስልጣኑ የራስ ሀይል አቅም እየተገነቡ እና ግንባታቸው እየተፋጠኑ ከሚገኙ መንገዶች መካከል ከጎፋ ካምፕ እስከ መብራት ሀይል ኮንዶሚኒየም የሚገነባው አንዱ ማሳያ መሆኑን አቶ ኢያሱ ገልጸዋል፡፡
ከእንግሊዝ ኤምባሲ ተነስቶ 22 እስከ ቦሌ ኤድናሞል የሚደርሰው የመንገድ ፕሮጀክት በዓለም ባንክ በጀት ድጋፍ በቻይናው ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ተቋራጭነት እንዲገነባ ከሁለት ዓመት በፊት ውል ተይዞ የተጀመረ ቢሆንም በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ አልነበረም፡፡ በዚህም ምክንያት ከፊሉ የመንገዱን አካል ተቋራጩ እንዲቀጥል ተደርጎ፤ ከጎላጎል እስከ ቦሌ ኤድናሞል ያለው መንገድ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ባለቤትነት ተይዞ እየተገነባ እንደሚገኝ አቶ ኢያሱ ለማሳያነት አክለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በራስ ሀይል መንገዶች ዳይሬክቶሬት የሰሜን አዲስ አበባ የመንገድ ግንባታ ስራ አስኪያጅ ኢንጂኒዬር ቢኒያም አለማየሁ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ በባለስልጣኑ እየተገነባ የሚገኘው ከጎላጎል እስከ ቦሌ መድኃኒዓለም ያለው የመንገድ ፕሮጀክት 2 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና ከ20 እስከ 30 ሜትር ስፋት አለው። መንገዱ በኮሪደር ልማት በተሰሩ መንገዶች ደረጃ የእግረኛ፣ የሳይክል፣ የተሽከርካሪ መንገዶችን፣ የታክሲ መጫኛ እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ዝርጋታን ታሳቢ ተደርጎ በቀን 24 ሰዓት ሳምንቱን በሙሉ እየተገነባ ይገኛል፡፡ የመንገዱ ፕሮጀክት በጥቅምት 2018 ዓ.ም በራስ አቅም የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አፈፃፀሙ 22 በመቶ ደርሷል፡፡ እስከ መጪው መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስም ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ