ሚዛናዊ ሀገራዊ ግንባታ ለልጆቻችን የምናወርሰው ስጦታ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ሚዛናዊ ሀገራዊ ግንባታ ለልጆቻችን የምናወርሰው ስጦታ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ጥር 16/ 2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት በዓል ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ሀገሪቱ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እና በወታደራዊ መስኮች የምታደርገውን ግንባታ በሚዛናዊነት በማሳደግ የተከበረች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማውረስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመርሐ-ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሀገሪቱ እያስመዘገበች ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ዘላቂ ለማድረግና ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ የሚዛናዊ ሀገራዊ ግንባታን አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ግዙፍ የልማት ሥራዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወኑ እንደሚገኙም አንስተዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ የ9.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስገንዘቧን እና የዘንድሮው የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም እንደሚያመለክተው ደግሞ በዓመቱ መጨረሻ ቢያንስ 10.3 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ ይጠበቃል ብለዋል።

ይህ ስኬት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር የተረጋገጠ መሆኑንና በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የልማት እንቅስቃሴ ከሚታይባቸው ሀገራት ተርታ እንደምትሰለፍም ጠቁመዋል።

በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪ እና በማዕድን ዘርፎች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ትርጉም የሚኖራቸው አስተማማኝ የፀጥታ ኃይል ሲገነባ ብቻ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም ኖሯቸው የፀጥታውን ዘርፍ ችላ ያሉ ሀገራት አሁን የሚገኙበትን አስቸጋሪ ሁኔታ እንደ ማሳያ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ጠንካራ የፀጥታ ኃይል ካልተገነባ የልማት ሥራዎቻችን ዋጋ አይኖራቸውም ብለዋል።

ሀገሪቱ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ እና በወታደራዊ መስኮች የምታደርገውን ግንባታ በሚዛናዊነት ማሳደግ እንዳለባት ጠቅሰዋል።

ይህ ሲሆን ብቻ የጸናች፣ የተፈራችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ማውረስ እንችላለን በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review