የጥራትና አቅርቦት መላ

You are currently viewing የጥራትና አቅርቦት መላ

መጋዘኑ ከምርት በኋላ የሚፈጠርን ብክነት ከመቀነስ ባለፈ የገበያ መረጋጋትን በመፍጠር ረገድም የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተመላክቷል

በምርት አያያዝ ጉድለት ምክንያት የሚጠፋው ሀብት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እያስከተለ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ። እንደ ዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) መረጃ፣ በዓለም ከሚመረተው ምግብ ውስጥ አንድ ሶስተኛው ወይም 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ቶን በየዓመቱ ይባክናል። ለዚህ ችግር ከሚጋለጡት የምግብ አይነቶች ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬዎች ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ ሲሆን፣ በየዓመቱ ከ40 እስከ 50 በመቶ ያህሉ ምርት በብክነትና በብክለት ሳቢያ ይጠፋል።

ወተትና ሥጋን ጨምሮ ሌሎች የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችም ለከፍተኛ ብክነት እንደሚጋለጡ የሚያትተው የፋኦ መረጃ፣ ከጥራጥሬ እና እህሎች ደግሞ ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆነው እንደሚባክን ያብራራል።

በፋኦ መረጃ መሠረት፣ ይህ የምግብ ምርት ብክነት ችግር በአፍሪካ ደረጃ ይከፋል። በአህጉሪቱ በቂ ቴክኖሎጂ እና ቀዝቃዛ መጋዘን ባለመኖሩ ብክነቱ ይብሳል፤ እስከ 50 በመቶ የሚሆነው የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ገበያ ሳይደርስ ይባክናል። ወተት በአግባቡ ባለመቀዝቀዙ ምክንያት እስከ 30 በመቶ የሚደርሰው ይባክናል። ከሰብልና ጥራጥሬም ከ20 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው በዋነኝነት በአያያዝ፣ በትራንስፖርትና በነፍሳት ምክንያት ይባክናል።

በኢትዮጵያ ደረጃም የምርት ብክነት መጠኑ እንደ ምርቱ ዓይነትና እንደየአካባቢው ቢለያይም፣ ችግሩ ግን ጎልቶ ይታያል። ከ30 እስከ 50 በመቶ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ከ20 እስከ 35 በመቶ የእንስሳት ተዋጽኦ እንዲሁም ከ15 እስከ 25 በመቶ ያህሉ ጥራጥሬና ሰብል እንደሚባክን የፋኦ መረጃ ያመላክታል። ባህላዊ ጎተራ መጠቀም፣ የነፍሳት ጥቃት፣ በወቅቱ አለመውቃት፣ የማቀዝቀዣ እጥረት፣ የትራንስፖርት እና የማሸጊያ ጉድለት ለብክነቱ የሚያጋልጡ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ በመረጃው ተመላክቷል።

ይህ ብክነት ኢትዮጵያ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር እንድታጣ ያደርጋታል። ብክነቱን መቀነስ ቢቻል፣ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ያግዛል ይላል የፋኦ መረጃ።

 የችግሩን አሳሳቢነት የተገነዘበችው ኢትዮጵያ አሁን አንዳች መላ ዘይዳለች። ይህም የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ማቀዝቀዣ መጋዘን መገንባቷ ነው። መጋዘኑ ከምርት በኋላ የሚፈጠርን ብክነትና ብክለትን ያስቀራል፤ የገበያ ማረጋጋትን በመፍጠር ረገድም ጉልህ ሚና ያለው ሲሆን፣ በተለይ የአትክልት፣ የፍራፍሬና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ለሸማቹ ማህበረሰብ እንዲሁም ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ረገድ የላቀ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።

 መጋዘኑ በ1 ነጥብ 75 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን፣ ከ11 ሺህ 437 ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ቦታ ላይ ያረፈ ነው። በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በአንድ ጊዜ ከ20 ሺህ ኩንታል በላይ አትክልትና ፍራፍሬ የመያዝ አቅም ያለው ነው ተብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ማቀዝቀዣ መጋዘን እና ሁለገብ ሕንፃ መርቀው ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፣ መጋዘኑ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግና ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ሀብት ነው።

መጋዘኑ በግዝፈቱ በኢትዮጵያ ቀዳሚ ስለመሆኑ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል። ይህ የማቀዝቀዣ መጋዘንና ሁለገብ ሕንፃ ከምርት በኋላ የሚፈጠርን ብክነትና ብክለትን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነውም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የተገነባው ይህ ዘመናዊ የማቀዝቀዣ መጋዘንና ሁለገብ ሕንፃ ለሀገሪቱ የንግድ ሥነ-ምህዳር የላቀ ፋይዳ እንዳለው ከኢፌዴሪ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያትታል። የንግድ ሥነ-ምህዳሩን ማዘመን፣ ምቹና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓት ማስፈን፣ የሎጂስቲክስ ስብራትን መጠገን፣ ንግድን የሚያሳልጥ ዘመናዊ መሠረተ-ልማት እንዲኖር ማድረግ፣ የአቅርቦት ሰንሰለት ስብራትን ለመጠገን ያለው አስተዋፅኦ ከሚሰጣቸው ጥቅሞች ጥቂቶቹ እንደሆኑም ተብራርቷል።

መጋዘኑን አስመልክቶ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሰጡት ሙያዊ ማብራሪያም ይህንኑ ሐሳብ የሚያጠናክር ነው። በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህር ለታ ሲራ (ዶ/ር) መጋዘኑ እንደ ሀገር ዘርፈ-ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት መምህር ለታ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ በአትክልት፣ በፍራፍሬ፣ በእንስሳት እና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በስፋት የምታመርት እንደመሆኗ እንዲህ ያለው ማዕከል ያስፈልጋታል ብለው፣ ጥራታቸው የተጠበቀ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ ንግድ ለማቅረብ የመጋዘኑ መገንባት በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

የግብርና ምርቶችን ምርታማነት ከፍ ለማድረግ ብክነትን መከላከል አንዱ አማራጭ ነው ብለው፣ ይህ መጋዘን ደግሞ ለገበያ የሚቀርቡ አትክልትና ፍራፍሬዎች እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ከብክነትና ብክለት ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ አይነተኛ ድርሻ አለው ብለዋል።

 ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት የማቀዝቀዣ መጋዘንና ሁለገብ ማዕከል ባለመኖሩ የሚያጋጥመውን ብክነት መገመት አያዳግትም ያሉት መምህር ለታ (ዶ/ር)፣ ለዚህም በአትክልት ተራዎች አካባቢ ለብልሽት ተዳርገው የሚጣሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በአብነት አንስተዋል። ይህ መጋዘን በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾችን ችግር ከመቅረፍ ባለፈ የግብርና ምርት እንዲያድግ፣ የዘርፉ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ፣ ብሎም የውጭ ምንዛሬን በማሳደግ ረገድም አበርክቶው የጎላ ነው ሲሉ አክለዋል።

እንደ መምህር ለታ (ዶ/ር) ገለጻ፣ በግብርና ምርቶች በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን ከሚያስችሉ ጉዳዮች መካከል እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው። ከምንም በላይ ደረጃውን የጠበቀ የምርት ማቆያ መኖር የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ ያስችላል፤ ስለዚህ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህ መጋዘን ለበርካታ ወገኖች የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ትኩስና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ያስችላል።

የገበያ መረጋጋትን ማረጋገጥ ሌላኛው የመጋዘኑ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ነው። ከፍተኛ ምርት በሚመረትበት ወቅት ከገበያ ፍላጎት በላይ የሆነውን ምርት በዘመናዊ መንገድ አቆይቶ በመያዝ፣ ለገበያው ዘላቂና ተከታታይ አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ የዋጋ መረጋጋትን ይፈጥራል።

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ስለመጋዘኑ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአትክልት፣ የፍራፍሬ እና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ለሸማቹ ማህበረሰብ እና ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ረገድ የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል ብለው፣ በተጨማሪም ሸማቹ ማህበረሰብ በተገቢ ዋጋ ትኩስ የግብርና ምርቶችን እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም፣ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የገበያ ሰንሰለቱን በማሳጠር ረገድም ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡ የከተማዋ አስተዳደር ለግብርና ምርት ጥራትና ተወዳዳሪነት አስፈላጊ የሆነው ይህ መጋዘን እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ይዞታ በማቅረብ ያደረገውን ድጋፍ በሌሎችም ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፡፡  

የአትክልት፣ ፍራፍሬ እና የእንስሳት ተዋጽኦ ማቀዝቀዣ መጋዘን በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ሰንሰለት ውስጥ ትልቅ ተስፋን የሰነቀ እርምጃ ነው። መጋዘኑ ከምርት በኃላ የሚፈጠርን ብክነት ከመቀነስ ባለፈ፣ የገበያ መረጋጋትን በመፍጠር ረገድም የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተመላክቷል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ እንደ ሕንድ፣ ኔዘርላንድስ እና ብራዚል ያሉ በግብርና የበለጸጉ ሀገራት የቀዝቃዛ መጋዘን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርና ምርቶቻቸውን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ረገድ ጠንካራ ልምድ እንዳላቸው የፋኦ መረጃ ይጠቁማል።

በኔዘርላንድስ የሚገኙ ዘመናዊ ማቀዝቀዣዎች ምርቶች ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ለወራት እንዲቆዩ በማድረግ፣ ሀገሪቱ በዓለም የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ቀዳሚ እንድትሆን አስችለዋታል። እነዚህ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት፣ የማቀዝቀዣ መሠረተ ልማት መኖር ማለት ምርት በወቅቱ ካለመሸጡ የተነሳ የሚፈጠርን የግዳጅ ሽያጭም ያስቀራል።

በአጠቃላይ፣ ይህ የቀዝቃዛ መጋዘን ፕሮጀክት ተራ መጋዘን ሳይሆን የግብርናውን ዘርፍ ወደ ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት የሚያሸጋግር ድልድይ ነው። ምርታማነትን ከገበያ ትስስር ጋር በማቀናጀት፣ ለአምራቹም ሆነ ለሸማቹ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ድባብ ይፈጥራል። ወደፊትም መሰል መሠረተ ልማቶች በስፋት ቢስፋፉ የሀገሪቱን የወጪ ንግድ አቅም በማሳደግ ረገድ ሚናቸው የጎላ ይሆናል።

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review