ሙዚቃ፡- ትውልድ ቀራፂው መምህር

You are currently viewing ሙዚቃ፡- ትውልድ ቀራፂው መምህር

በአብርሃም ገብሬ

የግሪኩ ፈላስፋ ፕሌቶ “ሪፐብሊክ” (The Republic) በተሰኘው መጽሐፉ “ሙዚቃ የሰው ልብ ውስጥ በጥልቀት ሰርጋ በመግባት የዜጎችን አስተሳሰብና ሥነ ምግባር የመግራት ኃይል አላት” ይላል፡፡ ጥሩ ሙዚቃ “የሕሊና ሚዛን በመሥራት ዜጎችን ታንጻለች፤ ጀግንነትንና ሚዛናዊነትን ትፈጥራለች” በማለት ያትታል። በእርግጥ ኪነ-ጥበብ፣ በተለይም ሙዚቃ፣ ወጣቶች ከማኅበራዊ ሚዲያ ጫጫታ ወጥተው ወደ ውስጣዊ ማንነታቸው እንዲመለከቱ እና ምክንያታዊ አስተሳሰብን እንዲያዳብሩ ትልቅ ድልድይ የመሆን አቅም አላት።

የኪነ ጥበብ ቁንጮ የሆነችው ሙዚቃ መልከ-ብዙ አቅምና ኃይል አላት፡፡ ለሰው ልጆች እርካታና ደስታን ትፈጥራለች፤ ማኅበራዊ ሕጸጾችን ትተቻለች፤ በብዙኃኑ ስምምነት ያገኘን ጉዳይ በሌላ አውታር በማሳየት መደመምን ትፈጥራለች፤ እንዲሁም ሰዎችን ታስተምራለች። ሙዚቃ የምታስተምረው ግን ቀጥታ አይደለም፡፡ ልክ በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በምንማረው ዘዴና አኳኋን ሳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ነው የምታስተምረው፡፡ “እኔ አውቅልሃለሁ” በሚል ዘይቤ ሳይሆን ተዝናኖትን በሚፈጥር መንገድ ነው በተዘዋዋሪ የምታስተምረው፡፡ በዚህ አምድም በፈረንጆቹ በወርሃ ጥር መጨረሻ ሳምንት እየተከበረ ያለውን የዓለም የትምህርት ቀን መነሻ በማድረግ ሙዚቃ ከትምህርት ጋር ያላት ጥብቅ ትስስር በፈርጅ በፈርጅ አድርገን በጨረፍታ እንቃኛለን፡፡

ሙዚቃ እንደ ስውር መምህር

ከወርሃ ጥር የመጨረሻ ሳምንት አንስቶ እስከ ወሩ ማብቂያ ድረስ በመላው ዓለም “ዓለም አቀፍ የትምህርት ቀን” ሆኖ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትምህርት ለሰላም፣ ለልማትና ለሰው ልጅ ነፃነት ያለውን የማይተካ ሚና ለማጉላት ነው ዕለቱ እንዲታሰብ የወሰነው። ትምህርት ሲባል ግን በክፍል ውስጥ የሚሰጥ መደበኛ ሥልጠና ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሰውን ልጅ አእምሮ የሚከፍት፣ አመዛዛኝ የሚያደርግና የሕይወት ዓላማን የሚያስጨብጥ የብርሃን ጉዞ ነው። በዚህ ጉዞ ውስጥ ደግሞ ሥነ-ጥበብ፣ በተለይም ሙዚቃ፣ እንደ ስውር መምህር ሆና ትውልድን በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ድርሻ አላት።

በሀገራችን ስለ ትምህርት አስፈላጊነትና ምንነት ከተቀነቀኑ ሙዚቃዎች ሁሉ የአንጋፋው ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ “ተማር ልጄ” የተሰኘው ሙዚቃን የሚስተካከል የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ጥቂት ስንኞች ከሙዚቃው ቀንጭበን እንመልከት፤

“ጊዜው ካፊያ ነበር

ትንሽ ጨለም ብሎ

አባቴ ሲጠራኝ እያለ ና ቶሎ

 ምንም ሕፃን ብሆን

ምስጢሩ ባይገባኝ

አባቴ እምባ አውጥቶ

አልቅሶ መከረኝ

ይገርማል…

ተማር ልጄ፣ ተማር ልጄ

ወገን ዘመድ የለኝ፣ ሀብት የለኝም ከእጄ፣

ስማኝ ልጄ፣ ሌት ፀሐይ ነው፣

ላልተማረ ሰው ግን፣

ቀኑም ጨለማ ነው…”

ሙዚቃው የሚጀምረው “ጊዜው ካፊያ ነበር፣ ትንሽ ጨለም ብሎ” በሚል ድባብ ነው። ይህ ዝናባማና ጨለምለም ያለ የአየር ሁኔታ፣ የአባቱን የውስጥ ስቃይና የሕይወት ትግል ይወክላል። ዝናብና ጨለማ በሥነ-ጥበብ ውስጥ ብዙውን ጊዜ “መከራን” ወይም “ያልተሳካ ሕይወትን” ለመግለጽ ያገለግላሉ። አባትየው በዚያ ድባብ ውስጥ ሆኖ ልጁን መጥራቱ፣ የሕይወት መኸር ሳያልፍበት ልጁ ከእሱ የተሻለ መንገድ እንዲይዝና በትምህርት ዕውቀት እንዲቀስም ከመሻት ነው፡፡

“አባቴ እምባ አውጥቶ፣ አልቅሶ መከረኝ” የሚለው ስንኝ፣ ትምህርት የደስታ ወይም የቅንጦት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያረጋግጣል። አባትየው የሚያለቅሰው ባለመማሩ የደረሰበትን ውርደትና መገፋት ልጁም እንዳይደግመው በመስጋት ነው።

“ምስጢሩ ባይገባኝ” የሚለው ሐረግ በተለይ ወጣቶች በመጀመሪያው የእድሜ ደረጃቸው የትምህርትን ፋይዳ እንደማይረዱ፣ ነገር ግን የወላጆች ምክር ከጀርባው ትልቅ የሕይወት ተሞክሮ እንዳለው ያሳያል።

“ወገን ዘመድ የለኝ ሀብት የለኝም ከእጄ”፤ ይህ ስንኝ የሙዚቃው ቁልፍ መልዕክት ነው። አባትየው ለልጁ የሚተውለት ርስት ወይም ገንዘብ እንደሌለው እየነገረው ነው። በዚህም ትምህርት እንደ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዋስትና ቀርቧል። ወጣቶች ራሳቸውን እንዲችሉና ከጥገኝነት እንዲወጡ ትምህርት የማይዘረፍ ሀብት መሆኑን ያስገነዝባል።

“ስማኝ ልጄ ሌት ፀሐይ ነው፣ ላልተማረ ሰው ግን ቀኑም ጨለማ ነው”

ይህ ስንኝ በአማርኛ የሙዚቃ ግጥም ውስጥ ካሉ እጅግ ድንቅ ስንኞች መካከል አንዱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለተማረ ሰው ሌሊቱ (ጨለማው) እንኳን በዕውቀቱ ብርሃንነት እንደ ፀሐይ ይበራለታል። ማለትም በክፉ ጊዜም ቢሆን መውጫ ቀዳዳ አያጣም። ላልተማረ ሰው ግን ፀሐይ በወጣችበት ቀን እንኳን፣ አእምሮው በድንቁርና ስለታወረ መንገዱ አይታየውም። ይህ ወጣቶች አመዛዛኝና አስተዋይ ካልሆኑ በምቾት ውስጥ ሆነው እንኳን ሕይወታቸው ስኬታማ እንደማይሆን ያስተምራል።

ሌላው ከመማር፣ ከማሰብና ከማስተዋል ጋር በተያያዘ ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃ ከሰጡን ሙዚቀኞች መካከል ዕውቋ ሙዚቀኛ አስናቀች ወርቁ ትገኝበታለች፡፡

“በል ተነሳ ልቤ፣ አስብ ተመራመር…

ተነስ ልቤ ተነስ፣ አትተኛ ገስግስ፣

እስክትገናኙ፣ እስክታየው ድረስ፣

 ሂድ ልቤ ተራመድ፣ በአንጎልህ ተመራ፣

 አያግድህ ዳገት አይግታህ ተራራ፡፡”

ከላይ የሰፈሩት የሙዚቃ ግጥም ስንኞች ከአስናቀች ወርቁ “መንገደኛው ልቤ” ከተሰኘው ሙዚቃዋ የተወሰዱ ናቸው፡፡ ሙዚቃው በተለይ የማሰብና የማመዛዘን ታላቅነት፤ በአእምሮ መመራት ያለውን ኃይል አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡

በአሁኑ ፈጣንና ግራ የሚያጋባ ዓለም ውስጥ ለሚገኝ ወጣት፣ ትልቁ የድል መሣሪያው ጡንቻው ወይም በደመ ነፍስ መነዳት ሳይሆን አእምሮው ነው የሚል ቅኝት አለው። የአስናቀች ወርቁ “መንገደኛው ልቤ” ሙዚቃ፣ ይህንኑ የአስተዋይነትና የምርምር ፋይዳ በግልጽ ያስቀምጣል። ሙዚቃው በደመ ነፍስ መነዳትን ወደ ጎን አድርጎ፣ በማስተዋል እና በዕውቀት መጓዝ ያለውን ጥቅም በአፅንዖት ያስገነዝባል።

“በል ተነሳ ልቤ አስብ ተመራመር” የሚለው ስንኝ፣ እያንዳንዱ ሰው የቸልተኝነት ወይም የልማዳዊ አሠራር አዙሪት እንዲወጣ የቀረበ ጥሪ አድርገን ልንተረጉመው እንችላለን። ማሰብ ማለት ዝም ብሎ መጨነቅ ሳይሆን፣ የችግሮችን ምንጭ መለየትና መፍትሔ መፈለግ ነው። “መመራመር” ደግሞ አንድን ነገር ከላይ ከላይ ከማየት ባለፈ፣ በጥልቀት መመርመርን ይጠይቃል።

አሁን ባለንበት ዘመን ዓለማችን በመረጃ ማዕበል ተጥለቅልቃለች። በተለይም ወጣቱ ክፍል የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚነቱ ከፍተኛ በመሆኑ፣ የዲጂታል ግርግር (Digital Noise) ሰለባ ሆኗል። ይህ ግርግር የወጣቱን የትኩረት አቅም ከመቀነሱም በላይ፣ ነገሮችን በጥልቀት የመመርመርና ምክንያታዊ የመሆን ብቃቱን እየተገዳደረው ይገኛል። በዚህ ፈታኝ ወቅት እንደ ሙዚቃ ያሉ የጥበብ ሥራዎች ወጣቱን ከውጭው ሁከት አላቅቀው ወደ ውስጠ-ሕሊናው እንዲመለስ፣ መጽሐፍትን እንዲያነብና ምክንያታዊ አስተሳሰብን እንዲያዳብር የሚያደርጉት አስተዋጽኦ የማይተካ ነው።

‘ዴሚ ለርኒግ’ የተሰኘ ገጸ-ድር በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2 ቀን 2025 “Art and Critical Thinking: Building Essential Skills Through Creative Expression” በሚል ባስነበበው መጣጥፍ እንዲህ ሲል አስፍሯል፤ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ማዳበር የሚጀምረው ካለማወቅ ሳይሆን፣ ከጥያቄ ነው። የጥበብ ሥራዎች ደግሞ ጥያቄን የመጠየቅ ጥበብን ያስተምራሉ። አንድ ሙዚቃ ሲደመጥ፣ ግጥም ሲነበብ ወይም አንድ ሥዕል ሲተነተን፣ ወጣቱ “ለምን?” እና “እንዴት?” የሚሉ ጥያቄዎችን እንዲያነሳ ይገፋፋዋል። ይህ በኪነ-ጥበብ አማካኝነት የሚዳብር የመጠየቅ ባህል ወደ ትምህርትና ንባብ ሲሸጋገር፣ ወጣቱ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያገኘውን መረጃ ሁሉ እንደ ወረደ ከመቀበል ይልቅ፣ በመረጃና በምክንያት መመዘን ይጀምራል።

በአጠቃላይ፣ ሙዚቃ ከጊዜያዊ ስሜትና መዝናኛነት ባለፈ፣ የትውልድ አስተሳሰብ የሚቀረጽበት ስውር መምህር ነች። ሙዚቃ ፕሌቶ እንዳለው ልብን የመግራት፣ አለማየሁ እሸቴ እንደዘፈነው የመማርን ፋይዳ የመግለጽ እና አስናቀች ወርቁ እንዳቀነቀነችው የአእምሮን መመራመር የማነቃቃት ታላቅ አቅም አላት። በመሆኑም፣ ሙዚቃን በቃናው ብቻ ሳይሆን በምስጢሩ፣ በዜማው ብቻ ሳይሆን በትምህርቱ ልናደምጠው ይገባል። ዛሬ የምንሰማው ሙዚቃ ነገ የምንሆነውን ሰው የመወሰን ኃይል አለውና።

ይሁንና የሃበሻ ኳየር መስራችና የኪነ ጥበብ ባለሙያው ቢተው ዳዊት እንደሚለው ሙዚቃን ጨምሮ ኪነ ጥበብ ሌሎችን የማስተማር፣ የማነቃቃትና የማስተባበር አቅሙ ጥልቅ ቢሆንም በልኩ ያልተነገረለት እና በስፋት ያልተሠራበት ዘርፍ ነው፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review