አዲስ አበባን ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ ያወዳጀው ልማት

You are currently viewing አዲስ አበባን ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ ያወዳጀው ልማት

የትናንቷ አዲስ አበባ ስፖርትን እንደ ሕይወት ዘይቤ ለመውሰድ ለሚፈልግ ሰው “አትሞክረው” የምትል ከተማ ነበረች። ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ለጤና ተብሎ የሚደረግ የእግር ጉዞም ሆነ የሩጫ እንቅስቃሴ ፈታኝ ነበር። ከተማዋ ለዓመታት ለስፖርት አፍቃሪዎች አንዳችም ምቾት የማይሰጥ ፊቷን ስታሳይ መቆየቷ ሳያንስ፣ ሰፈርና መንደሮቿ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት ነበረባቸው።

በእግረኛ መንገዶች ላይ የሚታየው የቆሻሻ መከማቸትና ንጽህናው ያልተጠበቀ አካባቢ፣ በነፃነት ለመተንፈስ እንቅፋት ነበር። በተለይም ከፋብሪካዎችና ከመኪናዎች የሚወጣው ጭስ አየሩን በመበከሉ፣ ስፖርተኛው ንጹህ ኦክስጅን ከማግኘት ይልቅ የተበከለ አየር ወደ ሳምባው ለማስገባት ይገደድ ነበር። ጠባብና የተቆፋፈሩ የእግረኛ መንገዶች ከተሽከርካሪዎች ግፊያ ጋር ተዳምረው፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አድካሚና አደገኛ አድርገውት ቆይተዋል።

ያቺ ስፖርተኞቿን የምትገፋና አቧራ የምታለብስ ከተማ ዛሬ ታሪኳን እየቀየረች ትገኛለች። አዲስ አበባ ዛሬ ላይ የውክቢያ ከተማ ከመሆን ወጥታ ነዋሪዎቿ በነፃነት የሚተነፍሱባትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እንደ ባህል የሚለማመዱባት ተስማሚና ምቹ ከተማ ለመሆን በቅታለች። ቀደም ሲል ከጭቃና ከጉድጓድ ጋር ይታገሉ የነበሩ እግረኞች፣ ዛሬ በደረጃቸው የተገነቡ፣ ሰፊና ምቹ የእግረኛ መንገዶችን አግኝተዋል። ይህም ለሩጫና ለፈጣን የእግር ጉዞ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ የብስክሌት ጋላቢዎችን መብትና ደህንነት የሚያስከብሩ መስመሮችን በማግኘቷ፣ ብስክሌት ከትራንስፖርት ባለፈ ለስፖርት በስፋት እንዲውል አድርጓል።

በየመንገዱ ዳር የተተከሉ አበቦችና ዛፎች የአየሩን ብክለት ከመቀነሳቸውም በላይ፣ ስፖርተኞች በሥነ-ልቦና ታድሰው እንቅስቃሴያቸውን እንዲያከናውኑ ረድቷቸዋል። ዘመናዊና ደማቅ የመንገድ መብራቶች በየኮሪደሩ መተከላቸው ነዋሪዎች እስከ ምሽት ድረስ በነፃነት ስፖርት እንዲሠሩ አግዟል። ይህም በተለይ በቀን ሥራ ለሚጠመዱ ግለሰቦች ትልቅ አማራጭ ሆኗል።

በሥራ ምክንያት ቀን ላይ ስፖርት ለመሥራት ጊዜ እንደሌለው የሚገልጸው የመዲናዋ ነዋሪ ወጣት ዳዊት ይገረም፣ ከዚህ ቀደም ማታ መሮጥ ቀርቶ በእግር መሄድ በራሱ ለደህንነት አስጊ እንደነበር ያስረዳል። “አሁን አዲስ አበባ ቀን ብቻ ሳይሆን በማታው ክፍለ ጊዜም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚደረግባት ሆናለች፤ መንገዶቿ በደማቅ መብራት ስለሚበሩ፣ ከምሽቱ 2 እና 3 ሰዓት ላይ ከጓደኞቼ ጋር እሮጣለሁ። የከተማዋ ጽዳትና ብርሃን ስፖርቱን አስደሳች አድርጎታል። ይህ ደግሞ ለሥራ መነሳሳትንና የአእምሮ እረፍትን ሰጥቶኛል” ሲል ያብራራል።

ይህ የመሠረተ ልማት ለውጥ የማኅበረሰቡን ሥነ-ልቦናም ቀይሮታል። ዛሬ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ መሮጥ እንደ እንግዳ ነገር መታየቱ ቀርቶ፣ የዘመናዊነትና የጤናማነት መገለጫ ሆኗል። ቤተሰቦች ከልጆቻቸው ጋር በፓርኮችና በሰፊ የእግረኛ መንገዶች ላይ ሲንቀሳቀሱ ማየት የተለመደ ትዕይንት ሆኗል። እዚህ ጋር የሦስት ልጆች እናት የሆኑትን ወይዘሮ ማኅደር ኃይሉን በምስክርነት እንጥቀስ።

“ልጆቼን ይዤ የምጫወትበትና የምሮጥበት ቦታ አጥቼ ነበር። አሁን ግን ቅዳሜና እሁድ ወደ ወዳጅነት ፓርክ ወይም እንጦጦ እንሄዳለን። ልጆቹ በነፃነት ይሮጣሉ፤ እኔም ከእነሱ ጋር እንቅስቃሴ አደርጋለሁ። ጽዱ አካባቢና አረንጓዴ ስፍራ መኖሩ ለልጆቹ የአካል እድገትና ለኛ ሰላም ትልቅ ትርጉም አለው” ብለዋል ወይዘሮ ማኅደር።

የከተማዋን የመንገድ ገጽታ የቀየረው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በተጨማሪ፣ ለስፖርት አፍቃሪዎች ትልቅ የምሥራች የሆኑት እንደ እንጦጦ ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ እና መሰል ልማቶች ናቸው። ሌሎች የኮሪደር ልማት ውጤቶች ለነዋሪው ክፍት የሆኑና ለስፖርት የሚጋብዙ ስፍራዎችን አበርክተዋል።

የእንጦጦ ፓርክ ለተራራ ላይ ሩጫ፣ ለብስክሌት ግልቢያ እና ለረጅም የእግር ጉዞ (Hiking) ተመራጭ ስፍራ ሆኗል። ወዳጅነት አደባባይም እንደዚሁ ሰፊ ክፍት ቦታዎች ያሉት በመሆኑ፣ በቡድን የሚሠሩ እንደ ዮጋ፣ ኤሮቢክስ እና የጠዋት ሩጫዎችን ለማከናወን ምቹ ሆኖ ተገንብቷል።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ ለከተማዋ አዲስ እስትንፋስ ስለመስጠቱ ዝግጅት ክፍላችን በስፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል። መታሰቢያውን ተከትሎ የተሠሩት ሰፊ አደባባዮች፣ ወጣቶችና አዳጊዎች የስኬቲንግ (Skating) እና የሰውነት ማጎልመሻ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ መመልከት የተለመደ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች የተገጠሙ ዘመናዊ መብራቶች ነዋሪው ከሥራ በኋላ እስከ ምሽት ድረስ በነፃነት እንዲሮጥና እንዲንቀሳቀስ አስችለዋል።

ቀደም ሲል ቆሻሻ ይጣልባቸው የነበሩ የወንዝ ዳርቻዎች ዛሬ አረንጓዴ ለብሰው ለእግር ጉዞና ለሩጫ ምቹ ወደሆኑ ስፍራዎች ተቀይረዋል። ይህም የከተማዋን አየር ጥራት በማሻሻል ስፖርተኛው ንጹህ ኦክስጅን እንዲያገኝ ረድቷል። እነዚህ የልማት ሥራዎች ‘ስፖርት ለጥቂቶች’ ብቻ የነበረውን አመለካከት ቀይረውታል። አሁን ላይ አዲስ አበባ በየመንገዱ ዳር በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የሚሮጡባት፣ ብስክሌት የሚጋልቡባትና ጤናቸውን የሚጠብቁባት ‘የስፖርት ከተማ’ እየሆነች መጥታለች ቢባል ማጋነን አይሆንም። ስፖርተኞች ተገቢ አመጋገብ እና ማገገምን ከመከታተል ጎን ለጎን፣ የሚሰለጥኑበትና የሚወዳደሩበት አካባቢ የሙቀት መጠን እና የአየር ብክለት ጉዳይም አሳሳቢ ስለመሆኑ የሚገልጹት ደግሞ ከፍተኛ የስፖርት ባለሙያው አቶ በኃይሉ በቀለ ናቸው።

“ቀደም ሲል ለስኳር ሕመሜ በእግር እንድጓዝ ሐኪም ቢያዝዘኝም፣ የምጓዝበት መንገድ አልነበረም። ወይ መኪና ይገፋሃል፣ ወይ ደግሞ አቧራውና የጭሱ መዓት ለሳምባ በሽታ የሚዳርግ ነበር። አሁን ግን ይህ የኮሪደር ልማት ለኔ ትልቅ በረከት ነው። ማልጄ ተነስቼ በሰፊው እግረኛ መንገድ ላይ ያለ ስጋት እራመዳለሁ። መንገዱ ዳር ያሉት አበቦችና ዛፎች የሚሰጡት መልካም መዓዛ ራሱ ልዩ ነው። አሁን መድኃኒቴን የቀነስኩ ያህል ነው የሚሰማኝ” የሚሉት ደግሞ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ኤሊያስ ይግዛው ናቸው።

በጽዳትና በስፖርት መካከል ያለውን ጠንካራ ቁርኝት ይበልጥ ለማሳየት ይረዳ ዘንድ አንዳንድ የጥናቶች መረጃ አቅርበን ጽሑፋችንን እንቋጭ። የዓለም ጤና ድርጅት ላለፉት 30 ዓመታት ጤናማ ከተሞች (Healthy Cities) በተሰኘው ንቅናቄው አማካኝነት የከተማ ንጽህና ለስፖርት ያለውን ፋይዳ ያስጠና ሲሆን፣ ጽዱ አየር እና ንጹህ የእግረኛ መንገዶች ባሉባቸው ከተሞች ነዋሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ ዕድላቸው በ20 በመቶ ይጨምራል።

የዓለም ጤና ድርጅት የአካባቢ፣ የአየር ንብረት ለውጥና ጤና ዳይሬክተር ማሪያ ኔራ (ዶ/ር) እንደሚሉት ከሆነም “ከተሞቻችንን ካላጸዳንና አረንጓዴ ካላለበስን፣ ነዋሪዎቻችንን ለስኳርና ለልብ ሕመም እየጋበዝን ነው” በማለት በከተማ ጽዳትና በስፖርት መካከል ያለውን ቁርኝት በጥናት አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰፈራ ፕሮግራም (UN-Habitat) በ2020 ባወጣው ሪፖርት የከተማ ጽዳት ለነዋሪዎች አካላዊ እንቅስቃሴ ያለውን ወሳኝነት እና ጽዱ ከተሞች ለስፖርት ምቹ በመሆናቸው ምክንያት በነዋሪዎቻቸው ላይ የሚታየውን የሕክምና ወጪ በከፍተኛ መጠን እንደሚቀንስ ያስረዳል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአማካይ 10 ሺህ እርምጃዎችን አልያም ቢያንስ 8 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆን ርቀትን በየዕለቱ መጓዝ የልብን ጤንነት ለማሻሻል፣ የደም ዝውውርን ለማሳለጥ፣ የአእምሮ ውጥረትን ለመቀነስ እና እንደ ስኳርና የደም ግፊት ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ትልቅ አቅም አለው።

እንደ ዓለም አካባቢ ጥበቃ ድርጅት መረጃ ከሆነም በአንድ ሺህ ከተሞች በአንዱ ውስጥ ብቻ 43 ሺህ ሰዎች የሚሞቱት በአረንጓዴ ቦታዎች እጦት እንደሆነ ይገልጻል። በእነዚሁ ከተሞች በአረንጓዴ ስፍራዎች እጦት ምክንያት 25 በመቶ ሰዎች ከስፖርት ውጪ ይሆናሉ ይላል።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review