AMN- ጥር 23/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል እና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ከጥር 23 – 25/2018 ዓ.ም ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚቆይ 17 ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል በኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፍቷል።
በፌስቲቫሉ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ አዲስ አበባ ከተማ ሁሉንም የልማት ዘርፎች ያማከለ የልማት አብዮት እያካሄደች ትገኛለች ያሉ ሲሆን በልማቷ ደግሞ ሁሉም እኩል የሚበለፅጉባት ከተማ ሁናለች ብለዋል።
አዲስ አበባ ለባሕልና ኪነ-ጥበብ በሰጠችው ልዩ ትኩረት ለዘርፍ የኪነ- ጥበብ ስራዎች ምቹ መሆኗን የገለፁት ምክትል ከንቲባው ይህም ኢትዮጵያዊያን ያለንን እምቅ ባሕል ለዓለም ሕዝብ ለማስተዋወቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ምቹ ሁናለች ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ለባሕልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው(ዶ/ር) በበኩላቸው አዲስ አበባ የሁሉም ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሕል ማሳያ መሆኗን ጠቅሰዋል።

ከተማዋ ኢትዮጵያውያን በባሕላቸው እንዲተሳሰሩ ብቻም ሳይሆን የዕድገታችን የብልፅግናችን መስፈንጠሪያም እንድትሆን ሌትተቀን እየተሰራ ነው ብለዋል።
ባሕሎቻችን ምግቦቻችን፣ ማጌጫ ልብሶቻችን ፣ የሕክምና ፈውሶቻችን እንዲሁም የኢንዱስትሪ መሠረቶችን ከመሆንም በላይ የዕድገታችን እና የሰላማችን መሠረት ጭምር እንዲሆኑ አበክረን እየሰራን ነው ሲሉ ቢሮ ሃላፊዋ ተናግረዋል ።
በፌስቲቫሉ ላይ የታደሙ ተሳታፊዎች ይህን መሠል መድረኮች መዘጋጀታቸው ውብ ባሕሎቻችንን ለአለም ሕዝብ ገልጦ ከማሳየት ባለፈ ለመጪው ትውልድም ማንነታቸውን አውቀው እንዲያድጉ የላቀ ሚና አላቸው ብለዋል።
በፌስቲቫሉ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፤ የሃይማኖት አባቶች፤ አባገዳዎች፤ ሀደ ሲንቄዎች፤ የዘርፉ ምሁራን፤ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች፤ ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
በታምሩ ደምሴ