የጠዋት ስፖርት፣ ለውጤታማ ቀን ምን ልዩ ፋይዳ አለው?

You are currently viewing የጠዋት ስፖርት፣ ለውጤታማ ቀን ምን ልዩ ፋይዳ አለው?
  • Post category:ጤና

AMN- ጥር 26/2018 ዓ.ም

በአሁኑ ወቅት ካለው ተለዋዋጭ የአኗኗር ዘይቤ እና ከሚታዩ የጤና ጫናዎች አንጻር፣ አብዛኞቹ የምንጋፈጣቸው ህመሞች ከእንቅስቃሴ ማነስ እና ከአመጋገብ ለውጥ ጋር የተያያዙ ሜታቦሊክ በሽታዎች ናቸው።

ይህንን ለመከላከል ደግሞ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን የዕለት ተዕለት ተግባራችን ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን የስኳርና የሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር ብሩክ አለማየሁ ያስረዳሉ።

ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የጠዋት ስፖርት ስላለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያብራሩት ባለሙያው፣ በአሜሪካ የኒውትሪሽን ሰርቬይ ሶሳይቲ እና የበሽታ መከላከልና መቆጣጠሪያ ማዕከል (CDC) ከ2003 እስከ 2006 ባደረጉት ጥናት፣ ስፖርት የሚሰራበት ሰዓት በሰውነት ክብደት (BMI) እና በወገብ ዙሪያ ስብ (Waist Circumference) ላይ ያለውን ተፅዕኖ አነጻጽረዋል።

በዚህም በማንኛውም ሰዓት ስፖርት መስራት የራሱ የሆነ ጠቀሜታ አለው ያሉት ባለሙያው፣ ይሁን እንጂ ጠዋት ላይ የሚሰሩ ሰዎች ከሌሎቹ በተሻለ ሁኔታ ከፍተኛ የክብደት መቀነስ እና የቦርጭ (የሆድ ውስጥ ስብ) የመቀነስ ውጤት አሳይተዋል።

ዶክተር ብሩክ እንደሚያብራሩት፣ ጠዋት ላይ ሰውነታችን ውስጥ የሚከሰቱ ተፈጥሯዊ የሆርሞን ለውጦች ለስፖርት እንቅስቃሴ እጅግ ተስማሚ ናቸው።

ጠዋት ላይ ‘ኮርቲሶል’ የተባለ ሆርሞን የሚጨምር ሲሆን፣ ወንዶች ላይ ደግሞ ‘ቴስቶስትሮን’ የተባለ ሆርሞን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል፤ ይህም ስብን ለማቃጠል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ጠዋት ስፖርት መስራት ወደ አእምሮ የሚሄደውን የደም ዝውውር ስለሚጨምር፣ አእምሯችን ቀድሞ እንዲነቃና ንቁ እንዲሆን ያደርጋል።

ሌሎች ገና ከእንቅልፋቸው በሚነሱበት ሰዓት፣ ስፖርት የሰራ ሰው ስነ-ልቦናዊ ዝግጁነቱ ከፍተኛ ስለሚሆን አስቸጋሪ ስራዎችን ለመጋፈጥና ውጤታማ ለመሆን ዝግጁ ይሆናል።

ምንም እንኳን ማታ ስፖርት መስራት ጡንቻን ለመገንባት የተወሰነ ጠቀሜታ አለው ተብሎ ቢታመንም፣ ክብደታቸውን መቀነስ ለሚፈልጉ እና ያልተመጣጠነ ውፍረት ላላቸው ሰዎች ግን ጠዋት መስራት ተመራጭ ነው።

ይህ ማለት ጠዋት ካልሰራችሁ ክብደት አይቀንስም ማለት አይደለም የሚሉት ዶክተር ብሩክ፣ አማራጭ እስካለ ድረስ ግን የጠዋት ስፖርት ለተሟላ ጤና እና ንቁ ውሎ ቁልፍ መሆኑን ይመክራሉ።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review