AMN- ጥር 27/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ ለዓመታት በመሰረተ ልማት እጥረት ሲቸገሩ ለነበሩ ነዋሪዎችና የንግድ ማህበረሰብ አባላት አዲስ የመነቃቃት መንፈስ እየፈጠረ ይገኛል።
በተለይም ከእንግሊዝ ኤምባሲ በጎላጉል አድርጎ እስከ ቦሌ የሚዘልቀው የኮሪደር ልማት ሥራ፣ የቀድሞውን አስቸጋሪ ሁኔታ በመቀየር ለነዋሪዎች ምቾትንና ለንግድ ሥራው ስታንዳርዱን የጠበቀ ዕድል ይዞ መምጣቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በየካ ክፍለ ከተማ እንግሊዝ ኤምባሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ መርሻ ሽፈራው ለኤ .ኤም ኤን እንደተናገሩት፣ ቀደም ሲል አካባቢው ለእግረኛም ሆነ ለተሽከርካሪ ምቹ ባለመሆኑ በንግድ እንቅስቃሴያቸው ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ቆይቷል።
መንገዱ ይሰራል ከተባለ ዓመታት ቢቆጠሩም ባለመጠናቀቁ ተስፋ ቆርጠው እንደነበር በማንሳት፣ አሁን ግን በኮሪደር ልማቱ መታቀፉ ዳግም ተስፋችን እንዲለመልም አድርጓል ይላሉ።
ግንባታው ሌት ተቀን እየተከናወነ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መርሻ፣ የአመራሩ የቅርብ ክትትል እና የሥራው ፍጥነት ቀደም ሲል የነበረውን እንግልት እንዲረሳ አድርጎታል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ተወዳዳሪነት እያላቀ ከመሆኑም ባለፈ፣ ነባሩንና አዲሱን የመሰረተ ልማት መስመር በማስተሳሰር ለንግድ ስራ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው።
ሌላው የአአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ መርዕድ ፈየ፣ ይህ መንገድ ከመገናኛ ፒያሳ እና ወደ ቦሌ የሚሄዱ መንገዶችን የሚያስተሳስር በመሆኑ አካባቢውን የንግድ ማዕከል ያደርገዋል ብለዋል።
የቀን ሠራተኛውም ሆነ ባለሙያው ሌት ተቀን እየሠሩ ነው ያሉት አቶ መርዕድ፣ የልማቱ መጠናቀቅ ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የልማቱ ተጠቃሚዎች መንግስት እያከናወነ ያለውን የልማት ስራ በመደገፍ የራሳቸውን ይዞታዎች ከኮሪደር ልማቱ ደረጃ ጋር እያስማሙ ይገኛሉ።
የንግድ የቤት ባለቤት የሆኑት አቶ ኪዳን ተስፋዬ፣ ልማቱ ሲጠናቀቅ የአካባቢው ገበያ እንደሚጨምርና ለሀገር የሚከፈለው ግብርም እንደሚያድግ ይናገራሉ።
ነዋሪዎችም የንግድ ቤቶቻቸውንና የመኖሪያ አካባቢያቸውን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በማሳመር የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የቦሌ መድኃኒዓለም፣ ጎላጉል እና እንግሊዝ ኤምባሲ የኮሪደር ልማት ሥራ በቀንና በሌሊት (24/7) በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ