AMN – ጥር 28/2018 ዓ.ም.
የአዲስ አበባ ከተማ የመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ማስጀመሩ አስተዳደሩ ለመምህራን ያለውን ክብር በተግባር ያሳየበት በመሆኑ መምህራን የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በ57 ማኅበራት ተደራጅተው፣ የሚጠበቅባቸውን 25 በመቶ ለቆጠቡ 6ሺህ194 መምህራን የመኖሪያ ቤት ግንባታ በትናንትናው ዕለት አስጀምሯል፡፡
መሬት ከሊዝ ነጻ እንዳቀረበና የፋይናንስ አማራጮችን እንዳመቻቸም የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡
መምህራን ቀደም ብሎ ሲነገር እውን ይሆናል ብለው እንዳልጠበቁና በተግባር ሲፈጸም መደሰታቸውን ለኤ.ኤም.ኤን ገልጸዋል፡፡

ለ30 ዓመታት በመምህርነት ያገለገሉት የሐምሌ 19 ቅደመ አንደኛና መጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት መምህሩ ብርሃኑ ከበደ፣ ቤት ለመምህር ከመኖሪያት በተጨማሪ አብዛሃኛውን የማስተማር ዝግጅት የሚያደርግበት በመሆኑ በተደጋጋሚ መንግሥትን ሲወተውቱ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይህ የመምህር ብርሃኑ ጥያቄም በርካታ መምህራን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲያነሱት የቆዩት ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም መምህራኑን የቤት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ የገባውን ቃልም ትናንት የቤት ግንባታውን በማስጀመር በተግባር አረጋግጧል፡፡
የዛሬዋን ቀን በጉጉት እጠብቃት ነበር ያሉት መምህር ብርሃኑ ከተማ አስተዳደሩ “የገባውን ቃል ለመፈጸም በቁርጠኝነት እንደሚሄድ አይቻለሁ” ብለዋል፡፡

መምህርት ዝግጁ ተመስገን ደግሞ መንግስት የገባውን ቃል በመፈጸም የቤት ግንባታው በመጀመሩ እጅግ ተደስቻለሁ ብለዋል፡፡
በቤት ጉዳይ ከኪራይ፣ ከቦታ ርቀት አንጻር የነበረባቸውን ችግር የሚቀርፍ መሆኑን የጠቀሱት መምህራኑ፣ ከተማ አስተዳደሩ ተስፋቸውን በማለምለም ለመምህራን ያለውን ክብር ያሳየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመምህራን ቤት ግንባታ እውን እንዲሆን፣ መንግስት ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ የካሳ ወጪ በመሸፈን፣ መምህራንን በማኅበር በማደራጀት፣ የዲዛይን ሥራዎችን በማከናወንና ኮንትራክተሮችን በመለየት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል፡፡
በታደሰ ሽፈራው