ቃል በተግባር

You are currently viewing ቃል በተግባር

“በመንግስትና የግል አጋርነት ወደ ግንባታ ሂደት የገቡ 97 ሺህ ቤቶች በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ
በትኩረት እየተሰራ ነው”

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

የቤት ባለቤት መሆን ለአንድ ሰው የኑሮ መረጋጋትን፣ ለከተማ ደግሞ የምጣኔ ሀብት ዕድገትንና ማህበራዊ ስኬትን ያጎናጽፋል። በአዲስ አበባ ከተማም እያደገ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና የአቅርቦት ልዩነት ለማጥበብ መንግስት የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ወደ ተግባር መግባቱ ይታወቃል። የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለከተማዋ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ባቀረቡት የ2018 ዓ.ም የመጀመሪያው 6 ወራት አፈፃፀም ሪፖርትም ከቤት ልማት ጋር በተያያዘ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ በከተማዋ በጀት፣ በመንግስትና በግል አጋርነት ሊገነቡ ከታቀዱ 100 ሺህ ቤቶች ላይ 97 ሺህ ቤቶች ወደ ግንባታ ሂደት የገቡ መሆኑን ጠቁመው፣ ሁሉንም በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በ65 ህብረት ሥራ ማህበራት ለተደራጁ 5 ሺህ 110 ቤት ገንቢዎች ጠንካራ ድጋፍ በመደረጉ 42 ማህበራት ወደ ግንባታ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ በግል እና ሪል እስቴት የሚገነቡ 13 ሺህ 517 የቤት ግንባታ ተከናውኗል፤ በኮሪደር የለሙ 810 የንግድ ቤቶችን በልማት ለተነሱ አነስተኛ ነጋዴዎች ማስተላለፍ መቻሉንም በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡

በመንግስት እና የግል አጋርነት ከ70 በላይ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ማስገባት የተቻለ ሲሆን፣ ከ1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር በላይ ካፒታል ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል፡፡ ለዚህ ስራ መሳለጥ የከተማ አስተዳደሩም ከ1 ሺህ 100 ሄክታር በላይ መሬት እና የመሰረተ ልማት አቀርቦት ተግባር ማከናወን መቻሉንም ገልፀዋል፡፡

ሰሞኑን የመምህራን የመኖሪያ ቤት ግንባታ በይፋ መጀመሩ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ተግባሩ የመምህራንን የቤት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ በከተማዋ ያለውን ከፍተኛ የቤት ፍላጎት ጫና በመቀነስ ረገድ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለመምህራን የመኖሪያ ቤት ህንፃ ግንባታን ባስጀመሩበት ወቅት፣ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

6 ሺህ 194 መምህራን በ57 ማህበራት በመደራጀት ወደ መኖሪያ ቤት ግንባታ ሂደት ገብተዋል፡፡ መምህራኑ ከጠቅላላው የቤቱ ዋጋ 25 በመቶ ቆጥበዋል፤ ይህ ቁጠባ 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ሲሆን፣ ቀሪውን 75 በመቶ በመንግሥት በኩል የብድር ሁኔታዎች መዘጋጀታቸውን ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አንስተዋል።

 “መምህራን ልብ ልትሉት የሚገባው ከተማዋ ያላትን ሀብት ሰጥታቹሃለች፤ ለልማት የቀረበው መሬት የከተማዋ ትልቁ ሀብት ነው፤ ይህም ለናንት ያለንን ክብር ያሳየንበት ነው” ብለዋል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 24 ቢሊየን ብር የሚያወጣ 40 ሔክታር የመኖሪያ ቤት ግንባታ መሬት በነፃ ለመምህራን ማቅረቡን ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ገልጸው፣ በካሳ መልክም 5 ቢሊዮን ብር መከፈሉን ተናግረዋል።

ለመምህራን የሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁና የአዲስ አበባ ከተማን ውበት የሚመጥኑ መሆናቸው የተመላከተ ሲሆን፣ መምህራን የቤት ባለቤት መሆናቸው የኑሮን ጫና በማቅለል ትውልድን የማነጽ ሥራ በአግባቡ ለመከወን እንደሚያስችላቸው ተገልጿል።

መምህራን ከሚያነሷቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች መካከል የቤት ጉዳይ አንዱ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ የከተማ አስተዳደሩም ለጥያቄው ምላሽ ሰጥቷል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ በተመሳሳይ፣ የመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ መጀመር መምህራኑ በየወቅቱ ሲያነሷቸው የነበሩ ጥያቄዎችን የመለሰ ነው ብለዋል፡፡

የመኖሪያ ቤቶች ግንባታው ሲነሳ ለቆየው የቤት ጥያቄ ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት የታለመ ስለመሆኑ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፣ ግንባታው በመንግስት ድጋፍና በማህበሩ ቅንጅት የሚከናወን መሆኑ ሂደቱን እንደሚያፋጥነው ተናግረዋል፡፡ አክለውም፣ የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ፍላጎት ጫና በመቀነስ ረገድም ትልቅ አቅም እንደሚኖረው አመላክተዋል።

አቶ ድንቃለም ጨምረው እንደገለፁት፣ ይህ ጅምር መምህራን በትምህርት ጥራት ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚሰጠው የስነ-ልቦና መረጋጋት ቀላል አይደለም፡፡

ቀደም ሲል በኪራይ መልክ ለመምህራን የተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ወደ ግላቸው እንዲያዞሩ መደረጉ እና ከዚህ ባለፈም ለመምህራን በየወሩ ይከፈል የነበረው የቤት ኪራይ አበል እንዲሻሻል መደረጉ ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ የጠቀሱት አቶ ድንቃለም፣ የመምህራኑን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት ሸገር እና አንበሳ አውቶብሶች ላይ ያለክፍያ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው መደረጉም ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመምህራን የመኖሪያ ቤት ግንባታ መጀመር የገባውን ቃል በተግባር አረጋግጦልናል ያሉት አቶ ድንቃለም፣ አያይዘውም በፍጹም በመምህራን አቅም የማይቻለውን የመሬት አቅርቦትና መሰል ጉዳዮችን መደገፉን ይገልጻሉ፡፡

በቤት ግንባታው ተጨባጭ እርምጃዎች መታየታቸው፣ በመምህራኑ ዘንድ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል። መምህራን እንደሚሉት፣ ይህ ፕሮጀክት መንግስት ለሙያው የሰጠውን ትልቅ ክብር ያሳያል። “ለሀገር ትውልድ የምንቀርጽ መምህራን እንደማንኛውም ዜጋ የተረጋጋ ኑሮ ሊኖረን ይገባል፤ አሁን የተጀመረው ስራ ይህንን ክብር የሚያረጋግጥ ነው” በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። የመምህራንን የቤት ግንባታ ለማከናውን የተደራጁ ማህበራትና ኮንትራክተሮችን በማገናኘት በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል የጋራ ስራ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) የተጀመረው የመምህራን የጋራ ቤት ግንባታ ያለምንም መስተጓጎል በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የተደራጁ ማህበራት ከኮንትራክተሮች ጋር በጋራ በመናበብና በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም ኮንትራክተሮች ቤቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ቃል በገቡት መሰረት በቅንጅት በመስራትና ስራውን በማጠናቀቅ ለመምህራን እንዲያስረክቡ አደራ የተጣለባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር እንጂኒየር ቶማስ ደበሌ በበኩላቸው፣ “ሀገር በተማረ የሰው ኃይል ይቀየራል” ብለው፣ “ይህንን የተማረ የሰው ኃይል ለሚያፈሩ መምህራን የሚሰራው የመምህራን የማህበር ቤት በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ኮንትራክተሮች ከተደራጁ ማህበራት ጋር በመስራት ለስራው ውጤታማነት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል” ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ማክሰኞ በ6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብስባ ላይ በሰጡት ማብራሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

ቤቶቹን በመንግስት፣ በግል፣ በመንግስትና በግል አጋርነት ለመገንባት ስራዎች መጀመራቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የባንክ፣ የዲዛይን፣ የመሬትና የፖሊሲ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ አክለውም፣ የግብዓት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ብረት፣ ሲሚንቶና ሌሎች ግብዓቶችን ለማምረት እየተሰራ ነው ብለው፣ በአዲስ አበባ ደረጃ የሚከናወኑ የመምህራን መኖሪያ ቤት ግንባታዎች የትልቅ ሀገራዊ ግብ አካል መሆኑንም መገንዘብ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ከመኖሪያ ቤት አቅርቦት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቤት አልሚዎችና ገዢዎች ከባንኮች ጋር በመዋዋል ቤት የሚያለሙበት የሞርጌጅ የአሠራር ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ አለመኖሩን በማንሳት ቤት አልሚዎችም ሆኑ ቤት ገዢዎች ሳይጎዱ ከባንኮች ጋር ተዋውለው ቤት የሚያገኙበትን አሠራር ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review