በአዲስ አበባ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን
- ለገቢ እድገቱ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱና የገቢዎች ቢሮ ተቋማዊ የመፈፀም አቅም ለማሳደግ የተሰራው ስራ
ተጠቃሽ መሆኑ ተጠቁሟ
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻም ሳትሆን የአፍሪካ መዲና፣ በዓለም ላይ ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት፡፡ አፍሪካውያን አንድነታቸውን ያወጁባት፣ በአህጉሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩባት፣ የሚወስኑባት ቤታቸው የሆነች ከተማ ነች፡፡
ሰሞኑን በስድስት የአፍሪካ ከተሞች ላይ በተደረገውና በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) ይፋ በሆነው ጥናት አዲስ አበባ በፋይናንስ አስተዳደር ቀዳሚ ከተማ መሆኗ ተረጋግጧል፡፡ ለሌሎቹ ከተሞችም ተሞክሮዋን አካፍላለች፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ጥናቱን ያደረገው በናይሮቢ፣ ኪጋሊ፣ ዳሬሰላም፣ ያውንዲ፣ አዲስ አበባ እና ሉሳካ ከተሞች ላይ ነው፡፡
አዲስ አበባ ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ልቃ የታየችበት አንደኛው ነጥብ በገቢ አሰባሰብ ወጪዋን በራሷ መሸፈን መቻሏ ነው፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ ከተሞች በብድርና ከፌዴራል መንግስት በሚያገኙት ድጋፍ ወጪያቸውን የሚሸፍኑ ሲሆን አዲስ አበባ 98 በመቶ ወጪዋን በራሷ ገቢ እየሸፈነች ትገኛለች። ቀሪውን ሁለት በመቶ በፌዴራል መንግስት አማካኝነት ለመጠጥ ውሃና ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ግንባታ በብድርና እርዳታ በሚገኝ ገቢ ነው የምትሸፍነው። ይህ ዓይነት አሰራር በሌሎች ከተሞች የማይታይ በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርጋት አቶ አብዱልቃድር ያስረዳሉ፡፡
የከተማዋ ገቢ ከዓመት ወደ ዓመት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ይገኛል፡፡ በ2010/11 በጀት ዓመት ከተማዋ 30 ቢሊዮን ብር ገቢ ትሰበስብ የነበረ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት ከ233 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችላለች፡፡ በ2018 በጀት ዓመት ደግሞ 350 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እየተሰራ ሲሆን ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ117 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በትናትናው እለት የአዲስ አበባ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት በመዲናዋ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወር 176 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 162 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን ከ92 በመቶ በላይ ገቢ ማሳካት ተችሏል፡፡ ይህ አፈጻጸም በ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት መሰብሰብ ከተቻለው ገቢ በ 51 ቢሊዮን ብር ወይም 45 ነጥብ 8 በመቶ እድገት እድገት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የከተማዋ ገቢ እያደገ የመጣበትን ምክንያት አቶ አብዱልቃድር ሲያብራሩ፣ “አዲስ አበባን መለወጥ ካለብን የከተማ አስተዳደሩን የማድረግ አቅም ማሳደግ አለብን በሚል በመሰራቱ ነው፡፡ የአስተዳደሩ የመፈፀም አቅም የሚያድገው ደግሞ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዳለ ሆኖ በጀትና ገቢን ማሳደግ ሲቻል ነው፡፡” ብለዋል፡፡
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፣ ከዚህ ቀደም የከተማዋን አቅም መሰረት አድርጎ የሚፈለገውን ገቢ ከማቀድ አኳያ ጉድለት ነበር፡፡ በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ከበጀት ውጪ ገቢ ላይ የሚሰራው ስራ ትኩረት ተሰጥቶት አይገመገምም ነበር። በአሁኑ ወቅት ከተማዋ ካላት አቅም አኳያ ሁሉም እየተሰበሰበ ነው ማለት ባይቻልም አዳጊ በሆነ መልኩ የገቢ እቅድን ማሳደግ እና የታቀደውን ማሳካት ላይ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያው የገቢ እቅድና አሰባሰብ ግብረ ሃይል በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እየተመራ ይገኛል፡፡ ግብረ ሃይሉ የፋይናንስ ቢሮ፣ የገቢዎች ቢሮ እንዲሁም ከፍተኛ ገቢ የሚሰበስቡ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ባለስልጣን፣ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮና ሌሎችም ተቋማት ያካተተ ነው፡፡
ለገቢ እድገቱ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱንና የአዲስ አበባ የገቢዎች ቢሮን ተቋማዊ የመፈፀም አቅም ለማሳደግ ጥረት ተደርጓል፡፡ የአሰራርና አደረጃጀት ሪፎርም ተደርጓል፡፡ ድሮ ሐምሌ ወር ላይ ግብር ሲሰበሰብ ግብር ከፋዩ ወረፋ ይዞ፣ ድንኳን ተደኩኖ፣ ፖሊስ ተመድቦ በእንግልት ነበር አገልግሎት የሚያገኘው። አሁን ያ ቀርቶ አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ ተደግፎ እየተሰበሰበ ይገኛል፡፡ የኦዲት ተደራሽነትን በማሳደግ፣ ውዝፍ እዳዎችን ተከታትሎ በመሰብሰብ፣ የቅሬታ አፈታት ስርዓቱን በማዘመን እና በግልፅነት በመስራት፣ ማበረታቻዎችን በመስጠትና ሌሎች ተግባራት መከናወናቸው በፈቃደኝነት ግብርን የሚከፍሉ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን አቶ አብዱልቃድር አስረድተዋል፡፡
አዲስ አበባ ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ጋር ተወዳድራ ውጤታማ ከሆነችባቸው መስፈርቶች መካከል ከምታገኘው ሀብት ወይም ከበጀቷ ምን ያህሉን ለካፒታል ፕሮጀክቶች ታውላለች የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ አኳያ አስቀድመን የበጀት እድገቱ ምን መልክ እንዳለው ማየት ያስፈልጋል፡፡ የአዲስ አበባ በጀት ከዓመት ወደ ዓመት እድገት እያሳየ መጥቷል፡፡ በ2010 በጀት ዓመት የከተማዋ በጀት 40 ነጥብ 5 ቢሊዮን የነበረ ሲሆን በ2011 በጀት ዓመት 44 ነጥብ 7 ቢሊዮን ነበር፡፡ በ2012 በጀት ዓመት 48 ነጥብ 6 ቢሊዮን፣ በ2013 በጀት ዓመት 61 ነጥብ 3 ቢሊዮን፣ በ2014 በጀት ዓመት 70 ነጥብ 6 ቢሊዮን፣ በ2015 በጀት ዓመት 113 ነጥብ 5 ቢሊዮን፣ በ2016 በጀት ዓመት 162 ቢሊዮን፣ በ2017 በጀት ዓመት 222 ነጥብ 5 ቢሊዮን ደርሷል፡፡
ምን ያህሉ ለካፒታል ወጪዎች ይውላል?
አቶ አብዱልቃድር በማብራሪያቸው፣ በርካታ የአፍሪካ ከተሞች ከሚይዙት በጀት ውስጥ አብዛኛውን ለመደበኛ ወጪ ነው የሚያውሉት፡፡ በዚህ ምክንያት ከተማን መለወጥ ላይ ጉድለቶች አሉ። አዲስ አበባ ከተማ ከጥቂት ዓመታት በፊት የምትሰበስበው ገቢ ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሆነው በጀት ለመደበኛ ወጪ ይውል ነበር፡፡
በ2015 በጀት ዓመት አዲስ አበባ ከምትይዘው በጀት ውስጥ 49 ነጥብ 37 የሚሆነው ለካፒታል ወጪዎች ሲውል ሌላው ለመደበኛ ወጪዎች (ደመወዝ፣ ስራ ማስኬጃና መሰል ጉዳዮች) ነበር የዋለው፡፡ በ2016 በጀት ዓመት ለካፒታል ወጪዎች የሚመደበው በጀት እድገት በማሳየት 64 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ ነበረው። በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ ከፍ ብሎ 71 ነጥብ 2 በመቶ ደርሷል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት ደግሞ 71 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆነው ዘላቂ ልማት የተያዘ ሲሆን በመጀመሪያው ስድስት ወርም 70 በመቶ የሚሆነው በጀት ለካፒታል ፕሮጀክቶች እንደዋለ የፋይናንስ ቢሮው ኃላፊው አቶ አብዱልቃድር ተናግረዋል፡፡
“የከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት ሰጪ ከተማ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ወጪ መናሩ የሚጠበቅ ነው፡፡ አገልግሎት ለመስጠት ቅርንጫፎችን መክፈት፣ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ማስደገፍና ሌሎች የተገልጋዩን እርካታ ለመጨመር የሚሰሩ ስራዎች ወጪ ይጨምራሉ፡፡ ነገር ግን የከተማ አስተዳደሩ ጠንካራ የሆነ የወጪ ቁጠባን ተግባራዊ በማድረግ አብዛኛውን በጀት ለካፒታል በጀት እንዲውል አድርጓል፡፡ ከካፒታል በጀት ውስጥም ሰው ተኮር ወይም የህብረተሰቡን ህይወት ለመለወጥ በሚያስችሉ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ውሏል” ይላሉ፤ አቶ አብዱልቃድር፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የደመወዝ ጭማሪ በመደረጉ በ2018 በጀት ዓመት የመደበኛ ወጪ ሊጨምር የሚችልበት ሁኔታ የነበረ ቢሆንም አብዛኛውን ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማዋል ተችሏል። ይህን ማድረግ የተቻለበትን ምክንያት ኃላፊው ሲያብራሩ፣ “የከተማዋን ገፅታ እና የነዋሪዎችን ህይወት መለወጥ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ቁርጠኝነት ከፍተኛ በመሆኑ የመደበኛ ወጪ ቅነሳ ላይ ተሰርቷል። የተቋማት አደረጃጀትን በመፈተሽ የማያስፈልጉት መዋቅሮች ማጠፍን፣ በሆቴል የሚደረጉ ስብሰባዎችን ማስቀረትን፣ የመንግስት ተሽከርካሪዎች ጥገናን በአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ከፍተኛ ወጪ መቆጠብ ተችሏል” ብለዋል፡፡
የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊው አቶ አብዱልቃድር እንደተናገሩት፣ አብዛኛው በጀት ለካፒታል ወጪዎቸ በመመደቡም በከተማዋ እድገት ላይ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ብዙዎች ከየት ሀብት አምጥታችሁ ሰራችሁት? እያሉ ይጠይቃሉ። ይህ የመጣው የውስጥ ገቢ ማሳደግ ላይ በመሰራቱና ከሚሰበሰበው ገቢም አብዛኛው ለልማት እንዲውል በመደረጉ ነው፡፡
በ2017 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስትና ህብረተሰብ ተሳትፎ ከ19 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት በቅተዋል። ሆስፒታል፣ ጤና ጣቢዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የስፖርት ሜዳዎች፣ የህፃናት መጫወቻዎች፣ መንገድና ሌሎች ልማቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል፡፡
በያዝነው በጀት ዓመት በግማሽ ዓመት ደግሞ 12 ሺህ 232 ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀዉ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ገልፀዋል።
አቶ አብዱልቃድር እንደተናገሩት፣ የከተማ አስተዳደሩ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖሩ፣ ያለውን ሀብት በጥብቅ ዲሲለፕሊን መመራቱ፣ ፕሮጀክት የማስፈፀም ብቃት ማደጉ በከተማዋ የሚታይ ለውጥ ማምጣት አስችሏል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ የሚያዘው በጀት በውጤታማነት ስራ ላይ እንዲውል፣ ሁሉን አቀፍ እድገት ማረጋገጥ እንዲቻል የህብረተሰቡን ጥያቄ ማዕከል መሰረት በማድረግ ይመደባል፡፡ የፕሮጀክቶች አፈፃፀም በጥብቅ ዲስፕሊን እንዲመሩ በማድረግ በተያዘላቸው ጊዜ ወይም አስቀድመው በጥራት ተሰርተው እንዲጠናቀቁ እየተደረገ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የኦዲት ግኝቶች በሪፖርት ከተገለፁ በኋላ ማስተካከያ ሳይደረግ ሼልፍ ላይ ነበር የሚቀመጠው፡፡ አሁን ግን በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አፈጉባኤ የሚመራ የኦዲት ፎረም ያለ ሲሆን በውስጥና በዋና ኦዲተር የወጣ ግኝት ሲገኝ ተቋማት ማስተካከያ እንዲያደርጉ ይደረጋል፡፡ ማስተካከያ ካላደረጉ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ ይህም ያለውን ሀብት አግባብ ባለው መልኩ ልማት ላይ እንዲውል አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል፡፡
ከሳምንት በፊት የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አዲስ አበባ ያስመዘገበችው የልማት ስኬት ሌሎች ከተሞች ተሞክሮ እንዲቀስሙበት የታለመ የውይይት መድረክ በከንቲባ ጽሕፈት ቤት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ በዚሁ ወቅት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ ከተማዋ የግብር አስተዳደርን በማዘመንና በዲጂታል መንገድ በመምራት ረገድ ባመጣችው ለውጥ የራስ ምንጭ ገቢዋን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ እንደቻለች ተናግረዋል።
ይህ ከፍተኛ የልማት በጀት በከተማዋ ገጽታ ላይ ብቻ ሳይሆን በዜጎች ስነ-ልቦና ላይ ያመጣው ለውጥ ግዙፍ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተሰሩት የኮሪደር ልማቶች፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች ግንባታ እና የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞች፣ ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል፣ ጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራ፣ የአረጋውያን ማዕከል እንደዚሁም የመኖሪያ ቤቶች ዕድሳትና ግንባታ ስራዎች የዚሁ የፋይናንስ አጠቃቀም ፍሬዎች ናቸው።
የአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር እንደገለፁት በአዲስ አበባ ከተማ በ2018 በጀት ዓመት 350 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወር 162 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን በቀጣይ ቀሪ ጊዜያትም የተያዘውን እቅድ ለማስፈፀም ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ