AMN—ግንቦት 5/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያና የፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከዛሬ 120 ዓመታት በላይ ፣ በይፋ ሲመሰረት፣ ዓላማው ሉዓላዊነትን በማስክበርና በምድር ባቡር ዝርጋታ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
ይህ ታሪካዊ ግንኙነት ዛሬ ላይ መልኩን ቀይሮ በአፍሪካዋ መዲና አዲስ አበባ እና በፈረንሳይዋ የብርሃን ከተማ ሊዮን መካከል ወደ ተጠነከረ የእህትማማች ከተሞች ስምምነት አድጓል።
በሺዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ቢራራቁም፣ አዲስ አበባና ሊዮን ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በከተማ ግንባታ ጥበብና በልማት ራዕይ ተሳስረዋል።
እ.ኤ.አ በ2005 የተጀመረው ይሄው የእህትማማችነት ቃል ኪዳን፣ ዛሬ ላይ አዲስ አበባ በምታከናውናቸው ሜጋ ፕሮጀክቶችና የኮሪደር ልማት ስራዎች ላይ አሻራውን በጉልህ እያሳረፈ ይገኛል።
ሁለቱ ከተሞች እ.ኤ.አ ከ2005 ጀምሮ ትኩረታቸውን በከተማ ፕላንና የዲዛይን ጥበብ፣ በታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃና እድሳት፣ በከተማ መብራት እንዲሁም በውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዘመናዊነት ላይ አድርገዋል።
በመሆኑም አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት የምትከተለውን ለሰው ልጅ ምቹ የሆነ የከተማ ግንባታ ፍልስፍና በመቅሰም ረገድ የሊዮን ሚና ከፍተኛ ነው። በተለይም በኮሪደር ልማቱ የተገነቡ ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መስመሮችና መናፈሻዎች የሊዮን ከተማን የዲዛይን ጥበብ የተከተሉ ተሞክሮዎች መሆናቸው ይነገራል።
ሌላው የሚጠቀሰው ስኬት የቆዩ ታሪካዊ ቤቶችን ሳይፈርሱ ይዘታቸውን ጠብቆ በማደስ ለቱሪዝምና ለንግድ ስራ እንዲውሉ የማድረግ ጥበብ ነው።
የሊዮን ከተማ አዲስ አበባን በሌሊት የምታስውብ የብርሃን ከተማ ለማድረግ የሚያስችለውን የቴክኒክ ጥናትና የባለሙያ ድጋፍ ከማድረጓም ባለፈ፣ በመቶዎች ለሚቆጠሩ የከተማ አስተዳደሩ ባለሙያዎች በፈረንሳይ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ የሰው ኃይል አቅም ግንባታንም እንዳደረገች ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡
ምንም እንኳን የሊዮን ከተማ በቴክኖሎጂ ድጋፍ የምትታወቅ ብትሆንም፣ አዲስ አበባም ለፈረንሳይ ባለሙያዎች ያበረከተችው አስተዋጽኦ የሚናቅ አይደለም። የአዲስ አበባ ፈጣን እድገትና መጠነ ሰፊ የከተማ ለውጥ ለሊዮን ከተማ “ፕላነሮችና አርክቴክቶች” አዲስ የሙያ ዕይታን ሰጥቷቸዋል።
የፈረንሳይ ባለሙያዎች ውስብስብ ችግሮችን በውስን በጀትና ጊዜን በመጠቀም እንዴት መፍታት እንደሚቻል ከአዲስ አበባ ተጨባጭ ተሞክሮ መውሰዳቸው ይነገራል።
በዲፕሎማሲው ረገድም ሊዮን የአፍሪካ መዲና ከሆነችው አዲስ አበባ ጋር ያላት ጥብቅ ግንኙነት በአውሮፓና በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተሰሚነት ከፍ አድርጎታል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሊዮን የሚያደርገው በረራና የሚያከናውናቸው የባህል ልውውጦች የከተማዋን የንግድና የቱሪዝም እንቅስቃሴ አነቃቅተዋል።
ዛሬ ላይ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የምናያቸው አረንጓዴ ስፍራዎች፣ ለእግረኛ ምቹ የሆኑ መንገዶችና የከተማዋ ድምቀት የእነዚህ የ20 ዓመታት ስኬታማ የወዳጅነት መደጋገፍ ፍሬዎች ናቸው።
በሁለትዮሽ ጥቅም ላይ የተመሰረተው ይህ ግንኙነት፣ በመጪው ጊዜም በዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድና በዲጂታል የከተማ አገልግሎቶች ላይ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
ታሪካዊው የኢትዮ-ፈረንሳይ ግንኙነት ዛሬ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ዘመናዊ መልክን ይዞ በተጨባጭ ለውጥ እያሳየ ይገኛል።
በአስማረ መኮንን