አፍሪካ ሆይ፤ ውብ አህጉሬ
በወርቅ የበለጸግሽ
በባህል የደመቅሽ
በነፍስ የታነጽሽ
ግን ለምንድ ነው ለዳቦ ሲሉ የሚሰደዱት ልጆችሽ?
ወንድሞቼ ሆይ ንቁ
እህቶቼ ሆይ ተነሱ
መሬታችን ሀብታችን ነው
አህጉራችን ዞረን የምንገባ
እናም የአባቶቻችንን ቤት እኛው እንገንባ… ትላለች ድምጻዊት ኡሙ ሳንጋሬ “ሞሱሉ” በተሰኘው አልበሟ ውስጥ አፍሪካን በተመለከተ በሰራችው ስራ፡፡
የአፍሪካ ሙዚቀኞች ትናንት ለነፃነት ድምጽ ሆነዋል፣ ዛሬ ደግሞ ለአንድነትና ለብልጽግና እየዘፈኑ ነው። ሙዚቃ የአፍሪካን መራራቅ የሚያፈርስ፣ መቀራረብንና አብሮነትን በዜማ የሚፈጥር ኃይል ሆኖ እያገለገለ ነው። ፓን አፍሪካኒዝምም በንግግር ብቻ ሳይሆን በከበሮ ምት፣ በዋሽንት ትንፋሽ፣ በሳክስፎን ድምፅና በግጥም ውስጥ ሕያው ሆኖ እየቀጠለ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካን ድምጽ ለዓለም ከሚያሰሙና የአህጉሩን አንድነት በሙዚቃ ስራዎች ከሚሰብኩ ሙዚቀኞች መካከል ፓን አፍሪካኒቷና የኢትዮጵያ ወዳጅ ኡሙ ሳንጋሬ ተጠቃሽ ነች፡፡
የኡሙ ሳንጋሬ ህይወትና ስራዎች
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ማሊ ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ የጥበብ ምልክቶች መካከል አንዷ የሆነችው ኡሙ ሳንጋሬ፣ የሙዚቃ ንግሥት ብቻ ሳትሆን የሴቶች መብት ተሟጋች እና የተሳካላት ፓን አፍሪካኒስት ናት። “የዋሳውሉ ንግሥት” በመባል የምትታወቀው ኡሙ፣ በዜማዎቿ የባህልን ውበት ከዘመናዊነት ጋር በማዋሃድ የአፍሪካን ድምፅ ለዓለም አሰምታለች።
እ.ኤ.አ. በ1968 በባማኮ የተወለደችው ኡሙ ሳንጋሬ የልጅነት ህይወቷ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ገና በሁለት ዓመቷ አባቷ ሌላ ሚስት አግብቶ ቤተሰቡን ጥሎ በመሄዱ፣ እናቷ አራት ልጆቿን ለማሳደግ ከፍተኛ ፈተና አይታለች። ኡሙ ሳንጋሬ ይህንን እናቷ የደረሰባትን መከራ እያየች ማደጓ፣ ለዛሬው የሙዚቃ ስራዎቿ እና ለሴቶች መብት ድምጽ እንድትሆን ትልቅ መነሳሳት ሆኗታል።
…የአፍሪካ ሴቶች ሆይ
ዓለምን በጀርባችሁ የተሸከማችሁ
መሬት የምታርሱ ፀሐይ እያቃጠላችሁ
እናንተ የታላቁ ዛፍ ስሮች ናችሁ።
ያለ ሴት፣ መንደሩ ጭር ያለ ፍርስራሽ ነው ወና
ሴትን አክብሩ እሷ የነገው ዓለም መገኛ ናትና… የሚለውን ስራዋን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡
ኡሙ ሳንጋሬ ሙዚቃን የጀመረችው ገና በልጅነቷ እናቷን ለመርዳት በየሠርጉ እና በየመንገዱ በመዘመር ነበር። በስድስት ዓመቷ በባማኮ በሚገኝ ትልቅ ስታዲየም ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች ፊት በመዘመር አስገራሚ ችሎታዋን አሳይታለች።
ድምጻዊቷ በዘመን ተሸጋሪ ስራዎቿ ዛሬም ድረስ የአፍሪካ ኩራት ሆና ቀጥላለች። ከምንም ተነስታ የዓለምን መድረክ መቆጣጠር እንደምትችል በተግባር አሳይታለች። ዜማዎቿ ጆሮን ብቻ ሳይሆን ልብን እና አእምሮን የሚያነቃቁ ናቸው። ኡሙ “ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ” በመሆን የታሪክ አሻራዋን በወርቅ ቀለም አስመዝግባለች።
ማሊያዊቷ የሙዚቃ ንግሥት ኡሙ ሳንጋሬ ከሀገሯ ድንበር ተሻግራ በመላው አፍሪካ አልፎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስም ካላቸው ከዋክብት አንዷ መሆን እና አህጉሯን ማስተዋወቅ ችላለች። ኡሙ፣ ሙዚቃን ለመዝናኛ ብቻ ሳይሆን ለማኅበራዊ ለውጥ፣ ለሴቶች እኩልነት እና ለአፍሪካ ኩራት መጠቀሚያ አድርገዋለች።
ታዋቂው ዘጋርዲያን ጋዜጣ ኡሙን “የማሊ የሙዚቃ ንግሥት” በሚል ርእስ ህይወትና ስራዋን የሚተነትን ዘገባ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ጋዜጣው በተለይ የእርሷን “Moussolou” አልበም 30ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሰራው ዘገባ፣ አልበሙ በአፍሪካ ሴቶች የነፃነት ትግል ላይ ያለውን ታሪካዊ ተጽዕኖ በዝርዝር አቅርቦታል።
ኔክስት ኢዝ አፍሪካ የተሰኘው ገጸ-ድር እ.ኤ.አ. በ2025 “Oumou Sangaré (Mali) The diva of Wassoulou” ሲል ባስነበበው ዘገባ በምታቀርበው ባህልን ያልዘነጋ ዘመናዊ ሙዚቃ ከባማኮ እስከ ከሲድኒ እና ፓሪስ ድረስ ተወዳጅ ሆናለች፡፡ በልዩ ድምጿና በአቀራረብ ለዛዋ የአፍሪካን መልክ ለዓለም በማሳየት እና ተከታታይነት ያለው ስኬት በማስመዝገብ ከዘመናዊው ዓለም ሙዚቀኞች መካከል ዋነኛዋ ሆኗ ቀጥላለች ሲል ገልጿታል፡፡
ኒው ዮርክ ታይምስ በበኩሉ ኡሙን “ዓለም አቀፍ ኮከብ” በማለት የገለጻት ሲሆን፣ በተለይም በትውፊት እና በዘመናዊነት መካከል ሚዛን በመጠበቅ ረገድ ልዩ ክህሎት ያላት ጥበበኛ መሆኗን መስክሯል፡፡ የእርሷ ሙዚቃ በምዕራቡ ዓለም አፍሪካን እንዴት በአዎንታዊ መልኩ እንደሚያስተዋውቅም ጋዜጣው በተደጋጋሚ ዘግቧል። እርሷም፡-
..ከካይሮ እስከ ኬፕ ታውን
ከዳካር እስከ አዲስ አበባ
አንድ መልክ ይታያል
አንድ ልብ ይመታል
አፍሪካዊ መሆን ኩራት ነውና
በታሪክ የታተመ፣ በማንነት የጸና….ትላለች በሙዚቃዋ፡፡ ኡሙ ሳንጋሬ ከአፍሪካ አልፋ የዓለም አቀፉ የሙዚቃ ሽልማት ግራሚ (Grammy Award) አሸናፊ መሆን የቻለች ድንቅ አርቲስት ናት። የእሷ አስተዋጽኦ ከዜማና ከቅኝት በላይ ነው። ለሴቶች ድምፅ መሆን፣ ባህልን ጠብቆ ማቆየት እና በአህጉሪቱ ላይ ተስፋን መዝራት የእሷ የሙዚቃ ስራዎች መገለጫ ናቸው። ዛሬም ድረስ ኡሙ ለአፍሪካ ኩራት እና ለጥበብ ሰዎች ትልቅ ትምህርት ቤት ሆና ቀጥላለች።
ኡሙ ሳንጋሬ በአዲስ አበባ
በእናቷ በኩል የኢትዮጵያ የደም ሐረግ እንዳላት የምትናገረው ኡሙ ሳንጋሬ፣ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ የእንጦጦ ፓርክን ጨምሮ የዓድዋ ድል መታሰቢያን፣ የመንገድ መሰረተ ልማትን፣ ፓርኮችን እና መሰል የልማት ስራዎችን ጎብኚታለች፡፡ በሰጠችው አስተያየትም “ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ከአምስት አመት በኃላ ነው። በከተማዋ በፍጥነት መለወጥ አስደንቆኛል” ስትል ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡
ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር እንዳላት የምትናገረው ኡሙ ሳንጋሬ (Oumou Sangaré) ዝም ብላ ድምፃዊት ብቻ አይደለችም፤ እሷ የአፍሪካ ነፃነት፣ የሴቶች መብት እና የአህጉሪቱ ባህል አምባሳደር ናት። ማሊያዊቷ የጥበብ ሰው፣ ለአፍሪካ ያበረከተችው አስተዋጽኦ በታሪክ ድርሳናት ውስጥ በጉልህ የሚሰፍር ነው። በተለይም የአፍሪካ መዲና ለሆነችው አዲስ አበባ ያላት ፍቅር እና ለከተማዋ የምትሰጠው ክብር ልዩ ቦታ አለው።
እውቅና እና ሽልማት
ኡሙ ለሙዚቃ እና ለማህበራዊ ለውጥ ላበረከተችው አስተዋጽኦ በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አግኝታለች። ከእነዚህ መካከል የግራሚ ሽልማት እ.ኤ.አ. በ2011 አግኝታለች፡፡ “Imagine” የተሰኘው ስራዋ ነበር ለዚህ ክብር ያበቃት፡፡ በተጨማሪም ለባህል እና ለሰላም ላበረከተችው አስተዋጽኦ ዩኔስኮ ኢንተርናሽናል ሙዚቃ ፕራይዝ ሽልማትን ተቀብላለች፡፡ ኮማንደር ኦፍ ዘ ኦርደር ኦፍ አርትስ ኤንድ ሌተርስ ደግሞ የፈረንሳይ መንግስት የሰጣት ክብርና ሽልማት ነው፡፡
ለብዙ ክብር የበቃችው ድምጻዊት ከሙዚቃ ዘርፍ ጋር በተያያዘ የአፍሪካ ወጣት ሙዚቀኞች የኪነ ጥበብ ስራቸውን በጥናት በተደገፉ የአህጉሪቷ የካበቱ እሴቶች ጋር በማጣመር የአፍሪካን መልክ ለዓለም ማስተዋወቅ እንዳለባቸውም ተናግራለች።
የአፍሪካ ሙዚቃ ቱባ ሀብት ያለው መሆኑን የምትናገረው ሳንጋሬ ይህን አቅም የአህጉሪቷ ታሪክ እና ትውፊት በሚያሳይ መልኩ መቅረብ እንዳለበት ታምናለች። ለዚህም ወጣት ሙዚቀኞች ከባህላቸው እና ከታሪካቸው ጋር እንዲቆራኙ የሚያደርጉ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ደጋግማ ትናገራለች፤ ትሰራለችም። በዚህም ኡሙ ሳንጋሬ ዛሬም ድረስ የአፍሪካ ኩራት ሆና ቀጥላለች።
በጊዜው አማረ