የአሁኑ ዘመን አርበኝነት ሀገርን በልማት መለወጥ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የአሁኑ ዘመን አርበኝነት ሀገርን በልማት መለወጥ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- የካቲት 11/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቄጦ የመስኖ መሠረተ ልማት ፕሮጀክትን መርቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአሁኑ ትውልድ ካለፉት አርበኞች ሊቀስመው የሚገባው ትልቁ ቁምነገር ሀገርን ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ነፃ የሚያወጣ የልማት አርበኝነት እንደሆነ ገልጸዋል።

እንደ አብዲሳ አጋ ያሉ ታዋቂ አርበኞችን ታሪክ በማስታወስ፣ እነርሱ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለጥቁር ሕዝብ ክብር መስዋዕትነት የከፈሉት ለሚመጣው ትውልድ ነፃና ኩሩ ሀገር ለማስረከብ እንደነበር አብራርተዋል።

ዛሬ ላይ ደግሞ ያንን የአርበኝነት መንፈስ ወደ ሥራና ምርታማነት በመቀየር የሕዝብን ሕይወት መለወጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አርበኝነት በጦር ሜዳ ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን በሥራ፣ በቴክኖሎጂ እና በልማት ሀገርን ማሳደግ ትልቁ የጀግንነት መለኪያ መሆኑን ጠቁመዋል።

አርበኞች በአድዋና በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ያሳዩት አንድነት ለዛሬው የብልጽግና ጉዞ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መከፋፈልን፣ መናናቅን እና ቂምን በመተው በጋራ ለሀገር እድገት መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ምሁራን ወጣቱን ወደ ልማትና ወደ ሰላም በመመለስ ረገድ የበኩላቸውን አደራ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

አርበኞች ነፃ ሀገር እንዳቆዩልን ሁሉ፣ የዛሬው ትውልድም ለነገዎቹ ልጆች የበለጸገችና የተመቸች ሀገር የማስረከብ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በቄለም ወለጋ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የኮሪደር ልማትና ሌሎች የመሠረተ ልማት ጅማሮዎች የሚበረታቱ መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህ የልማት ጠብታዎችን ወደ ባህር እንዲያድጉ መላው ሕዝብ በንቁ ተሳትፎና ለሰላም እንዲቆም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት ውስጥ በአካባቢው በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት ህዝቡ ከታደለው የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም ሳይችል መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።

አካባቢው በቡና፣ በከብት እርባታ እና በሰብል ምርት የታወቀ ቢሆንም፣ የሰላም እጦት ለልማት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።

ህዝቡ ሰላምን ይወዳል፣ ሰላምን የፈጣሪ ልጅ ብሎ ይቀበላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አለመግባባቶች ሲኖሩም በሽምግልና እና በውይይት የመፍታት የቆየ ባህልን መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይም የትጥቅ ትግል መርጠው የነበሩ ወንድሞች የህዝቡን ጥሪ ሰምተው ወደ ሰላም መመለሳቸውን አድንቀው፣ የቀሩትም ይህንን አርአያ ተከትለው እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሁሉም ዜጋ በአንድ ልብና በአንድ ሀሳብ ለሀገር ልማትና እድገት እንዲቆም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review