AMN- የካቲት 13/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያውያን ወራሪውን የጣሊያን ጦር በተባበረ ክንድ ድል በመንሳት፣ ነጮች የጥቁሮች የበላይ ነን ብለው ያጸኑት ኃያልነት የተናደበት ልዩ ክስተት ነበር። ኢትዮጵያ ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ቀንዲል የሆነውን ደማቅ ታሪክ አድዋን ጻፈች። አድዋ የጦርነት ድል ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ፍልስፍና (ፓን-አፍሪካኒዝም) መሠረት ነው።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን በቴክኖሎጂና በኃይል ዓለምን ሲያሸብሩ፣ ጥቁር ሕዝብ ነጭን ማሸነፍ አይችልም የሚል የተሳሳተ ትርክት በዓለም ላይ ቢነግስም፣ የአድዋ ድል ይህንን የስነ-ልቦና እስር ቤት ሰብሮ ጥሏል።
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪው ዳግማዊ ተስፋዬ (ዶ/ር) የአድዋ ድል መላው አፍሪካውያንን የሚወክልና የሚያስተሳስር የድል ጮራ መሆኑን ያነሳሉ።
ከአድዋ ጀግኖች የምንማራቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ አንዱ፣ ጽኑ አንድነት ነው የሚሉት የታሪክ መምህሩ፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሙሉ ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድ ዓላማ የቆሙበት የታሪክ አደባባይ ነው። የሰሜኑ፣ የደቡቡ፣ የምስራቁ እና የምዕራቡ ሰው በዘር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት ሳይከፋፈል “ሀገሬ” ብሎ ወጥቷል። ልዩነቶችን አቻችሎ ለጋራ ብሔራዊ ግብ እና ለሀገር ሉዓላዊነት በጋራ መቆም ለድል ቁልፍ መሆኑን ይነግረናል።

የማይበገር የሥነ-ልቦና ጥንካሬ መገንባት
ዶክተር ዳግማዊ በወቅቱ ጣሊያን ዘመናዊ መሣሪያና የሰለጠነ ጦር ይዞ ቢመጣም፣ አርበኞቻችን ግን የታጠቁት “ለሀገሬ እሞታለሁ” የሚል የላቀ የሞራል ስንቅ ነበር። ለነፃነት ያላቸው ፍቅር ከጥይትና ከመድፍ በላይ ጠንካራ መሆኑን አስመስክረዋል። ማንኛውንም ታላቅ መሰናክል ለማለፍ ቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን የውስጥ ጥንካሬና ለራስ ክብር መስጠት ወሳኝ መሆኑን ያሳዩበት እንደነበረ አንስተዋል።
የዛሬው ትውልድም ቢሆን በድህነት፣ በበሽታ ወይም በሌሎች ተግዳሮቶች ተሸንፎ “አልችልም” ከሚል ስሜት ወጥቶ፣ ከራስ መተማመን በመነሳት ተራራን መናድ እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል ብለዋል።
አርበኞቻችን ወደ አድዋ ሲዘምቱ ከማንም የውጭ ኃይል እርዳታ አልጠበቁም፤ የራሳቸውን ስንቅ አዘጋጅተው፣ በቅሎ ጭነው፣ መሣሪያ ይዘው ነው የተጓዙት ያሉት ዶክተር ዳግማዊ፣ ይሄ ራስን የመቻል ታላቅ ማሳያ ነው በማለት ገልጸዋል።
ይህ ደግሞ የሀገር እድገትና ክብር የሚመጣው በልመና ሳይሆን በራስ ድካምና ጥረት መሆኑን ያስገነዝበናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አክለውም ዛሬም ቢሆን አንዲት ሀገር በምግብ ራሷን ካልቻለችና በዕርዳታ የምትኖር ከሆነ፣ ሉዓላዊነቷና ክብሯ ሙሉ ሊሆን እንደማይችል ያስተምረናል ብለዋል።

የኢኮኖሚ ነፃነትን ማረጋገጥ
አባቶቻችን በጦር ሜዳ የሀገርን ሉዓላዊነት አስከብረዋል፤ የዛሬው ትውልድ ደግሞ ሀገሪቱን ከልመና እና ከዕዳ ጥገኝነት የሚያላቅቅ የኢኮኖሚ አድዋ ላይ ማተኮር አለበት ሲሉ ይመክራሉ። አክልውም የኢኮኖሚ ነፃነት ማለት አንድ ሀገር በሌሎች ጫና ወይም ትእዛዝ ሳይሆን፣ በገዛ ሀብቷና አቅሟ የራሷን የኢኮኖሚ ውሳኔ የመወሰን አቅም ሲኖራት ነው።
ለአድዋው ትውልድ ይህ ማለት የባዕድ ቀንበርን አለመቀበል እንደነበረው ሁሉ፣ ለዛሬው ትውልድ ደግሞ በልመና እና በዕዳ አለመገዛት መሆን አለበት ብለዋል።
ይቅርባይነትና ለጋራ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት
ከአድዋ ጦርነት በፊት በነበሩት ዓመታት በመሳፍንቱና በንጉሡ መካከል ብዙ አለመግባባቶች ነበሩ፣ ነገር ግን የሀገር ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ የነበረውን ቂምና በቀል ወደ ጎን በመተው ለጋራ ጠላት በአንድነት ቆመዋል። ይህ ደግሞ በልዩነቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ለትልቅ ሀገራዊ ግብ ሲባል ይቅርታ እና ትብብር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ ያሳየናል ነው ያሉት።
የአድዋ ድል የታላቅነታችን ምስጢር ብቻ ሳይሆን፣ የግል እና የቡድን ፍላጎትን ለሀገር ክብር አሳልፎ የመስጠት ጥበብ የታየበት የታሪክ ምዕራፍ ነው።

ጥበብና ስልታዊነት
የአድዋ ድል በጭፍን ጀግንነት ብቻ የተገኘ ሳይሆን በዲፕሎማሲ፣ በስለላና በወታደራዊ ስልት የታጀበ ነበር።
አባቶቻችን የጠላትን እንቅስቃሴ በማጥናትና የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ጠላትን ድል አድርገዋል፤ ይህም ለዘመኑ ችግሮች በስሜት ብቻ ሳይሆን በዕውቀት፣ በብልሃትና በጥልቅ ስልት መፍትሔ መፈለግ እንዳለብን ያስተምረናል ብለዋል።
ዶክተር ዳግማዊ አድዋ የጡንቻ ብቻ ሳይሆን የአእምሮ ድል ነው። ትውልዱ ዛሬ የሚገጥሙትን የኢኮኖሚ፣ የሰላም እና የቴክኖሎጂ ተግዳሮቶች ለማሸነፍ እንደ አባቶች ልብ ያለው ጀግና እና ጭንቅላት ያለው ትውልድ መሆን እንዳለበት እንደሚያስተምር ገልጸዋል።
የዛሬ ትውልድ የራሱን ታሪክ ከመጻፍ አንፃር የአድዋ ድል ያለፈ ወታደራዊ ድል ብቻ ሳይሆን፣ ለሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሕያው እሴት ላይ የተመሠረተ ንድፍ እንደሆነ መረዳት አለበት ነው ያሉት፡፡
አድዋ አልቻልንም የሚለውን የሽንፈት መንፈስ የሰበረ ድል መሆኑን በማንሳትም፣ ዛሬም ትውልዱ ካለበት የድህነትና የክፍፍል ቀንበር ለመውጣት እንደ አድዋ አርበኞች በአንድነት እና በጥበብ መነሳት ይኖርበታል ሲሉ ነው የታሪክ ምሁሩ አጽንዖት የሰጡት።
በቶለሳ መብራቴ