AMN- የካቲት 17/2018 ዓ/ም
ኢትዮጵያ ለሰባተኛ ጊዜ ለምታካሂደው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅቷን እያጠናከረች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በምርጫው ለመሳተፍና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አካል ለመሆን ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።
ቀደም ባሉ ጠቅላላ ምርጫዎች ላይ ተሳትፎ የነበራቸው ነዋሪዎቹ፣ የዘንድሮውን ምርጫ በንቃትና በልዩ ዝግጅት እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል።
ለኤ ኤም ኤን አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ዋለልኝ አያሌው፣ ባለፉት ምርጫዎች ላይ ተሳታፊ እንደነበሩ አስታውሰው፣ አሁን ደግሞ የምርጫው ጊዜ ሲቃረብ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣትና ለሀገር ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መወሰናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ሁሴን አህመድ በበኩላቸው፣ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ተሳታፊ እንደነበሩና አሁን ለሚካሄደው ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ተመሳሳይ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በምርጫ ሂደት ውስጥ የሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እና የውጤት አቀባበል ያላቸውን ፋይዳ የገለጹት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ብስራት ጫንያለው፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሥልጣን ሽግግር በዲሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
የመረጥኩት ፓርቲ ባያሸነፍ እንኳ ውጤቱን በፀጋ እቀበላለሁ ያሉት አቶ ብስራት፣ ከሁከትና ከግርግር ይልቅ ሰላማዊ ውይይትና የሕዝብን ድምፅ መቀበል ለሀገር ግንባታ እንደሚበጅ አስገንዝበዋል።
ያሸነፈው አካልም ሆነ ያልተመረጠው ወገን ለአንድ ሀገር የጋራ ዓላማ በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም ጨምረው ገልጸዋል።
ወይዘሮ አሚናት ይመር በበኩላቸው፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት ዜጎች በቂ መረጃ የማግኘት ችግር እንደነበረባቸው አስታውሰው፣ አሁን ላይ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችሉ መድረኮች መመቻቸታቸውን ተናግረዋል።
ይህም ዜጎች የሚፈልጉትን ፓርቲ ፕሮግራም አውቀው እንዲመርጡ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ በተለይ አዲስ አበባ ላይ የታየው የዲሞክራሲ ልምምድ ከበፊቱ ብዙ ትምህርቶች የተወሰዱበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ስኬታማ እንዲሆን እያንዳንዱ ዜጋና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚገባቸው ተመላክቷል፡፡
በበረከት ጌታቸው