AMN -የካቲት 19/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል የምርት አቅርቦትን በመጨመር፣ የገበያ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት እና የንግድ ስርዓት ህጋዊነትን በማስፈን ዉጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
የሰብል ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የዳልጋ ከብት፣ በግና ፍየልን ጨምሮ የድጐማ ምርቶች የሆኑት ዳቦ፣ የምግብ ዘይትና ስኳር በተመጣጣኝ ዋጋ ለመዲናዋ ነዋሪዎች በመቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከገበያ መሰረተ ልማት ጋር በተያያዘም በአምስቱም የከተማዋ የመግቢያ በሮች ከተሰሩ የገበያ ማዕከላት በተጨማሪ የላፍቶ ቁጥር ሁለት ገበያ ማዕከል ወደ አገልግሎት እንዲገባ በማድረግ የደላላን ሰንሰለት መበጣጠስ፣ የግብይት መዳረሻዎችን ማስፋት እና ደረጃቸዉን ማስጠበቅ ተችሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በሁሉም ክፍለ ከተሞች 245 የቅዳሜ እና የእሁድ ገበያ ማዕከላትን በመክፈት ነዋሪዎች በአቅራቢያቸው ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምቱ ማድረግ ተችሏል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የንግድ ስርዓት ህጋዊነትን ከማስፈን አንጻርም ከ230 ሺህ በላይ የንግድ ድርጅቶች የበር ለበር ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ ህገ-ወጥነትን የመከላከል ስራ አከናዉኗል፡፡
በሂደቱም 12ሺህ 139 ጥፋተኛ የሆኑ ነጋዴዎችን በመለየት አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን 10ሺህ 496 ያህሉ ወደ ህጋዊነት ተመልሰዋል፤ ቀሪዎቹም በሂደት ላይ ናቸው፡፡
በመዲናዋ ከተሰሩ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ጋር ተያይዞ የምሽት ንግድ እንቅስቃሴን ጨምሮ የመዲናዋ የግብይት ስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመነ ይገኛል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ