AMN – የካቲት 25/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን በቦሌ በሻሌ 40/60 ኮንዶሚኒየም የሚገኙ ከ6 ሺህ በላይ አባወራዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ነዋሪዎቹን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ከአራብሳ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ያከናወነ ሲሆን 6.7 ኪ.ሜ የመካከለኛ መስመር ዝርጋታና 3 ባለ 800 ኪቮአ፣ 12 ባለ 630 ኪቮአ፣ 30 ባለ 1250 ኪቮአ በአጠቃላይ 45 ትራንስፎርመር ተከላ ማከናወኑን አገልግሎቱ ገልጿል፡፡
ነዋሪዎቹ ካሁን በፊት ባለ ሶስት ፌዝ ቆጣሪ በጋራ ይጠቀሙ እንደነበር ያስታወሰው አገልግሎቱ፣ በዚህም በኃይል እጥረትና በኃይል መቆራረጥ ምክንያት ሲቸገሩ ቆይተዋል ብሏል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በተከናወነው የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ዝርጋታ ለእያንዳንዳቸው ቆጣሪ ተገጥሞላቸው ያልተቆራረጠ ኤሌክትሪክ ማግኘት መቻላቸውንም ገልጿል፡፡

ሪጅኑ ባከናወነው የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ዝርጋታ በበሻሌ ኮንዶሚኒየም ነዋሪ የሆኑ 6ሺ 700 አባወራዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንደሆኑም ተመላክቷል፡፡
በተያያዘም ሪጅኑ በተለያዩ አካባቢዎች የነበረውን የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ ከአራብሳ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የሚነሱ አዳዲስ ወጪ መስመሮች ዝርጋታ አከናውኗል፡፡
ዝርጋታቸው የተከናወነው ወጪ መስመሮች እያንዳንዳቸው ከ6.5 ኪሜ በላይ ርዝመት ያላቸው ሲሆን ሁለቱ ባለ 33 ሺህ ቮልት፣ ሶስቱ ደግሞ ባለ 15 ሺህ ቮልት መሆናቸውን አገልግሎቱ ገልጿል፡፡
በወጪ መስመሮቹ ዝርጋታ ከፍተኛ የኃይል ጭነት የነበረባቸው 3 ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ማለትም የወረገኑ፣ገጣፎ እና ቦሌ ለሚ ሁለት ተንቀሳቃሽ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል እንዲቀነስ በማድረግ የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሹን ለመቀነስ፣ አዳዲስ ደንበኞችን ለማስተናገድ ተጨማሪ አቅም መፍጠር መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ ገልጿል፡፡